ኢትዮጵያ በአፍሪካ ግዙፉን የአየር ማረፊያ በ12 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር እየገነባች ነው – ሲ ኤን ኤን

You are currently viewing ኢትዮጵያ በአፍሪካ ግዙፉን የአየር ማረፊያ በ12 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር እየገነባች ነው – ሲ ኤን ኤን

AMN ሚያዝያ 15/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ከ12 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ በአፍሪካ ግዙፉን እና ትልቁን የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ መጀመሯን ሲ ኤን ኤን ዘግቧል።

በታዋቂው የዛሃ ሀዲድ አርክቴክትስ የተነደፈው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት፣ በጥር ወር 2018 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት ሲሆን ግንባታውም በፈጣን ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል።

ፕሮጀክቱ ከ12 ነጥብ 5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነባ ሲሆን የመጀመሪያው ምዕራፍ እ.ኤ.አ. በ2030 ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ 60 ሚሊዮን ተሳፋሪዎችን የሚያስተናግድ ሲሆን፣ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ደግሞ 110 ሚሊዮን ተሳፋሪዎችን የመቀበል አቅም ይኖረዋል።

በአፍሪካ ግዙፉ የአየር ማረፊያ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት በምትገኘዉ በቢሾፍቱ ከተማ በመገንባት ላይ ይገኛል።

አዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ አህጉራዊ ፋይዳው የጎላ ሲሆን የአፍሪካ ከተሞችን ከማስተሳሰር ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ አለዉ።

ኢትዮጵያን የአህጉሪቱ ዋና የትራንስፖርት ማዕከል እንደሚያደርጋትም ታምኖበታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፕሮጀክቱን “በአፍሪካ ታሪክ ትልቁ የአቪዬሽን መሰረተ ልማት ግንባታ” ሲሉ መግለጻቸዉ ይታወሳል።

ቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ የኢኮኖሚ እና የቱሪዝም እድገት አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ሲ ኤን ኤን በዘገባዉ አካቷል።

ከዚሁ ከቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ለአውሮፕላን ማረፊያው ፕሮጀክት የሚውል የገንዘብ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በዋሽንግተን ዲሲ አድርጋለች።

በመድረኩ ላይ ኢትዮጵያ ለቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ከአሜሪካ መንግሥት ተቋማት፣ከታዋቂ የፋይናንስ ተቋማት እና ከዘርፉ ግዙፍ ኩባንያዎች ጠንካራ ድጋፍ አግኝታለች።

ድጋፉ በአፍሪካ ግዙፍ ከሆኑ የአቪዬሽን መሠረተ ልማቶች አንዱ የሆነውን ይህን ፕሮጀክት እውን ለማድረግ እንደሚያስችል ተመላክቷል።

ከፍተኛ የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት ኢትዮጵያ ግልጽነት የሰፈነበትና በግል ዘርፉ የሚመራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ለጀመረችው የሪፎርም ጉዞ ያላቸውን ጽኑ ድጋፍና እምነት ገልጸዋል።

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review