ከህልም ወደ ተግባር – አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌታዊ ጉዞ በላቀ ምዕራፍ ላይ

You are currently viewing ከህልም ወደ ተግባር – አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌታዊ ጉዞ በላቀ ምዕራፍ ላይ

AMN-ሚያዝያ 16/2018 ዓ.ም

የሀገራችን የቱሪዝም ዘርፍ በ”ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም” ማዕቀፍ ውስጥ የኢኮኖሚ እድገታችን ዋነኛ ምሰሶ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

በ”ገበታ ለትውልድ” መርሃግብር የተከናወኑ የልማት ስራዎች የተፈጥሮ ጸጋዎቻችንን ከዘመናዊ ጥበብ ጋር በማቀናጀት ለኢትዮጵያ አዲስ ገጽታና ክብር እየገነቡ ነው።

እነዚህ ፕሮጀክቶች ታሪካዊ እሴቶቻችንን ጠብቆ ለትውልድ ከማሻገር ባለፈ፣ ኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንትና የሁነት ቱሪዝም ተመራጭ መዳረሻ በማድረግ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት በተግባር እያረጋገጡ ነው።

ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የእርዳታ ጥገኝነትን ታሪክ ለመቀየር የጀመረችው መጠነ-ሰፊ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።

በመስኖ ልማትና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የተመዘገቡት ስኬቶች ሀገራችን ራሷን ለመመገብ የጀመረችው ጉዞ የማይቀለበስ መሆኑን ያበስራሉ።

ይህ የልማት እንቅስቃሴ ከታዳሽ ኃይል አቅርቦት ጋር ተሳስሮ እየተከናወነ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ያላትን ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪነትና የኮፕ32 ጉባኤን በላቀ ብቃት የመምራት ዝግጁነቷን በተጨባጭ እያሳየች ትገኛለች።

የከተሞች እድሳትና የዜጎችን ክብር የመመለስ ስራችን “ሰው ተኮር” ልማትን ማዕከል ባደረገ መልኩ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ዘመናዊ የስፖርትና የመዝናኛ መሰረተ ልማቶችን ከኢኮኖሚ እድሎች ጋር በማቀናጀት፣ የጀግኖቻችንን ታሪክ እየዘከርን ለተተኪው ትውልድ ምቹና ዘመናዊ ከተሞችን እየገነባን እንገኛለን።

እነዚህ ፕሮጀክቶች የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወት ከማሻሻላቸው ባለፈ፣ የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ የሚያፋጥኑና የከተሞቻችንን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያረጋግጡ ናቸው።

በሳይንስና በምርምር ዘርፍ የተገነቡት የላቁ ማዕከላት በጤናው ዘርፍ ራሳችንን ለመቻልና ብሄራዊ ደህንነታችንን ለማጽናት የተያዘው ግብ ስኬታማ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው።

ምርምርን ወደ ተግባራዊ መፍትሔ በመቀየር የዜጎችን ደህንነት ማረጋገጥና የኢኮኖሚ እድገታችንን በዕውቀት መምራት የመንግስት ዋነኛው ትኩረት ነው።

በአጠቃላይ በሁሉም ዘርፎች የተመዘገቡት የተቀናጁ ድሎች ኢትዮጵያ ወደ ታላቅነቷ የምታደርገው ጉዞ የተሳለጠ መሆኑን የሚያረጋግጡ በመሆናቸው፣ ይህን አገራዊ ራዕይ ዳር ለማድረስ በጋራ መቆም የወቅቱ ዋነኛ አጀንዳችን ነው።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review