በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ዜጎችን ህይወት ከመቀየር ባሻገር

You are currently viewing በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ዜጎችን ህይወት ከመቀየር ባሻገር

AMN – ሚያዝያ 20 /2018 ዓ.ም

አዲስ አበባን ምቹና ውብ ለማድረግ የተከናወኑና ተግባራዊ የተደረጉ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ፣ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ የልማት ስራዎች ነዋሪዎች ጤናማ አኗኗርን እንዲጎናጸፉ እያስቻሉ ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ስራዎች ከተማዋን የለውጥ ምሳሌ አድረገዋታል።

የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ የልማት ስራዎች፣ ዘመናዊ የመብራትና የቴሌኮም እንዲሁም ፍሳሽ መስመሮች እንዲዘረጉ አስችሏል ፣ ለጤና ምቹ ከባቢን ፈጥሯል ፣ የትራንስፖርት ስርዓትን አሳልጠዋል ፣ ባጠቃላይ መዲናዋን የዘመነች ዓለም አቀፍ ተመራጭ ከተማ የማድረህ ሂደትን ያፋጠኑ ሆነዋል።

በአዲስ አበባ እየተካሄዱ ያሉ ልማት ፕሮጀክቶች የመዲናዋን ገጽታ መቀየር ብቻ ሳይሆን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ዜጎችን ህይወት ያሻሻሉ ናቸው፡፡ ልማቶቹ ጎስቋላ አኗኗንር በማስወገድ ፣ በዝቅተኛ ገቢ ያሉ ነዋሪዎች ጭምር የተሸለ ምቹና ደረጃውን የጠበቀ አኗኗን እንዲጎናጸፉ እያደረጉ ናቸው።

በመዲናዋ ለኑሮ ተስማሚ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሁለንተናዊ ጠቀሜታ ያላቸው ሥራዎች ሲከናወኑም ከመንግስት ጥረት በተጨማሪ ባለሃብቶች፣ በጎ ፈቃደኞችና ህዝቡ በንቃት ተሳትፏል፡፡

በአዲስ አበባ የሚሰሩ መሰረተ ልማቶች ሰው ተኮርና ሁሉንም ዜጎች ያቀፉ ለመሆናቸዉ ፣ ለህዝብ ጥቅም የዋሉ በርካታ መኖሪያ አካባቢዎች ምስክር ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት በጎስቁልናው ይታወቅ የነበረው አዋሬ ፣ አሁን የአካባቢውን ነዋሪዎች ያቀፈው ልማት ወደ እጅግ ምቹ ና ለመኖር ተመራጭ አካባቢነት ተቀይሯል።

በከተማዋ በተለያዩ ሥፍራዎች የተከናወኑ መሰል መልሶ ግንባታዎች ፣ ምቹ የመኖሪያ ቦታን ፣ የንግድ ሥፍራን ፣ አረንጓዴ የመዝናኛ ሥፍራዎችን በመፍጠር የዜጎችን የዘመናት ችግር እያቃለሉ ይገኛሉ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ግንባታውን ያስጀመሩት ፣ የቅጠል ተራ ቤት ግንባታ ፕሮጀክትም የከተማ አስተዳደሩ እየሰራበት የሚገኘው ጉስቁልናን በምቾት የመቀየር ታላቅ ራዕይ አካል ነው።

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቅጠል ተራ አካባቢ የተጀመረው የቤት ግንባታ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ዜጎችን ህይወት ከመቀየር ባሻገር በአዲስ አበባ ከተማ ስማርት ሲቲን ከመመስረት አኳያ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ይታመናል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የግንባታ ሥራው መጀመሩን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልእክት ÷ በቅጠል ተራ የተጀመረው የቤት ግንባታ 10 ሺህ ካሬ ላይ ያረፈ ነው፡፡

ግንባታው ሲጠናቀቅም ከ20 ሺህ በላይ ሰዎችን ንፁህ ፣ ለሰው ክብር የሚመጥን ዘመናዊ አኗኗር ያለው መኖሪያ ቤት ተጠቃሚ የሚያደርግ ይሆናል።

ፕሮጀክቱ ልጆች ቦርቀው እንዲያድጉ የስፖርት ሜዳ እንዲሁም የንግድ ሱቆች እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ሁሉ ተሟልተውለት በጥራት እና በፍጥነት ተገንብቶ እስከ አዲስ ዓመት እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።

ያኔ ጎስቋላዋ ቅጠል ተራ ፣ ለአካባቢው ነዋሪዎች እና ለሌሎችም የምትተረፍ እጅግ ምቹ ፣ የዘመነችና ጤናማ የመኖሪያ እና የንግድ መንደር ትሆናለች።

በሻምበል ምሕረት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review