AMN – ሚያዝያ 25/2018 ዓ/ም
ዛይድ የደግነት ሩጫ የ5 ኪሎ ሜትር ውድድር ለአትሌሎች አዲስ የውድድር አማራጭ የፈጠረ እና የገቢ ምንጭ እድልም ይዞ የቀረበ መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዚደንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን ገለጹ፡፡
መነሻ እና መድረሻውን መስቀል አደባባይ አድርጎ የተከናወነውን ዛይድ የደግነት ሩጫ የ5 ኪሎ ሜትር ውድድር አስመልክቶ ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን ፣ ዛይድ የደግነት ሩጫ ውድድር የደግነትና የመደጋገፍ አላማን የያዘ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ለአትሌሎች አዲስ የውድድር አማራጭ ይዞ የቀረበ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በውድድሩ ታዋቂ አትሌቶች እንደተሳተፉ እና ለአሸናፊዎች የ600 ሺህ ብር ሽልማት መበርከቱንም በመጥቀስ ለአትሌቶች የተሻለ ጥቅም የሚስገኝ እንደሆነ አብራርተዋል።
ታላቁ ሩጫ፣ የኢትዮጵያ ታምርት የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር እና በየክልሎች የሚዘጋጁ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮች ለአትሌቶች የውድድር አማራጭ ሆነው የቀረቡ ናቸው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ይህም ለአትሌቶች ገቢ ከማስገኘት ባለፈ የተለየ እድል ይዞ የመጣ መሆኑን ጠቅሰው እንደዚህ ዓይነት ውድድሮች መስፋት እንዳለባቸው አመላክተዋል፡፡
አትሌቲክስ የኢትዮጵያ ሃብት በመሆኑ ዘርፉን ለማሳደግ በትኩረት መስራት አስፈላጊ ነው ያሉት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ፤
የትራክ እና ሌሎች ውድድሮች ላይም ፌደሬሽኑ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን አንስተው ፤ የጎዳና ላይ ውድድሮችን በማስፋት ልክ እንደሌሎች ሃገራትም ሐገርን ለማስተዋወቅ እንደሚረዳ ተናግረዋል።
የሻምበል ምህረት