AMN – ሚያዝያ 25/2018 ዓ/ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን የአምራች ዘርፍ ለማስፋፋት የሚደረገውን ጥረት የሚያጠናክረውን አራተኛውን ‘ኢትዮጵያ ታምርት’ ኤክስፖ 2018 ዛሬ በይፋ መርቀው ከፍተዋል።
የአምራች ዘርፉ ግብዓት አቅርቦት በዓመት ከ9 ሚሊየን ወደ 15 ሚሊየን ቶን ማደግ፤ ለአዳዲስ የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንቶች ከ3 ነጥብ 4 ጊጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል መቅረብ ኤክስፖው እስካሁን ያሳያቸው እና የተመዘገቡ ዋና ዋና ስኬቶች ናቸው፡፡
ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚቀርበው የፋይናንስ አቅርቦት ከ8 ነጥብ 1 ቢሊየን ወደ 50 ቢሊየን ብር ያደገ ሲሆን ለከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ደግሞ ከ262 ቢሊየን ብር በላይ ከፍ ብሏል፡፡ ለዘርፉ ከ2 ነጥብ 28 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ተመድቧል፡፡

እንዲሁም የፋብሪካዎች የማምረት አቅም ከ47 በመቶ ወደ 67 በመቶ ማደጉ፤ የማምረት አቅምና ዕድገት ከ4 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 10 ነጥብ 7 በመቶ ከፍ ማለቱ የተገለጸ ሲሆን በቀጣይም ተጨማሪ ዕድገት እንደሚጠበቅ ተጠቁሟል፡፡
ምርትን በሀገር ውስጥ በመተካት እስከ 4 ነጥብ 85 ቢሊየን ዶላር ማዳን የተቻለ ሲሆን የወጪ ንግድም ከፍተኛ እድገት እያሳየ ይገኛል፡፡
ከ2 ሺህ 800 በላይ ኢንቨስትመንቶችን መሳብ እንደተቻለ እና ለ1 ነጥብ 4 ሚሊየን ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩንም ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ኤክስፖው ኢንዱስትሪዎችን የሚያስተሳስር፣ ኢንቨስትመንትን የሚስብ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ አምራቾችንና በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ጎብኚዎችን የሚያገናኝ ቁልፍ ሀገራዊ መድረክ ሆኗል።
በአጠቃላይ የኤክስፖው መከፈት የአምራች ዘርፉ ለኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ያለውን ፋይዳ በማጉላት የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ሽግግር እያፋጠነ መሆኑን ያሳያል።