የሀገር ባለውለታዎችን በህይወት እያሉ የመዘከርና የመደገፍ ተግባር

You are currently viewing የሀገር ባለውለታዎችን በህይወት እያሉ የመዘከርና የመደገፍ ተግባር

AMN- ሚያዝያ 26/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ጥቂት ዓመታት የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለሀገር ሉዓላዊነትና ለገጽታ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሀገር ባለውለታዎች የሚሰጠውን እውቅና እና ድጋፍ አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ተግባራዊ እያደረጋቸው የሚገኙት የኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶችና ሌሎች ሰው ተኮር መሰረተ ልማቶች ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ ከማድረግ ባለፈ የሀገር ባለውለታዎች በህይወት እያሉ በክብር የሚዘከሩባቸውን መድረኮች ተካተውባቸዋል።

ለጀግኖች የሚሰጥ የላቀ ክብር ከለውጡ ማግስት ጀምሮ መንግስት የሀገርን ደህንነት በጽናት ለጠበቁ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት፣ ለአባትና እናት አርበኞች፣ በዓለም አደባባይ የኢትዮጵያን ስም ላስጠሩ አትሌቶችና ለኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ልዩ ትኩረት ሲሰጥ ቆይቷል።

ታዲያ ይህ ተግባር በቃላት ከሚገለጽ ምስጋና ባለፈ የመኖሪያ ቤት ስጦታዎችን በማበርከትና ዘላቂ መታሰቢያ የሚሆኑ ሀውልቶችን በማቆም በተግባር ተገልጿል።

የኢትዮጵያን እና የአባት አርበኞችን ታሪክ የያዘው ግዙፉ የዓድዋ ድል መታሰቢያ መንግስት ለታሪክና ለጀግኖች የሰጠው ትልቅ ቦታ ማሳያ ሆኗል።

እንዲሁም በተለያየ ጊዜ ለመከላከያ ሰራዊት አባላትና ለቤተሰቦቻቸው የመኖሪያ ቤት ስጦታዎች የተበረከተ ሲሆን በቅርቡ የተመረቀውና ለስፖርት ቤተሰቡ ልዩ ትርጉም ያለው “አዲስ ስፖርት ፓርክ” ኢትዮጵዊያን በላባቸውና በአጥንታቸው ላቆዩ አትሌቶች የተሰጠ ትልቅ ስፍራ ነው።

ፓርኩ በውስጡ በዓለም የኦሎምፒክ መድረክ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ በማድረግ የወርቅ ሜዳልያ ያስገኙ 15 ጀግና የአትሌቲክስ ፈርጦችን የሚዘክር ሀውልቶችን በውስጡ ይዟል።

በተመሳሳይ የሀገሪቱን ቱባ ባህልና እሴት በኪነ-ጥበብ ስራዎቻቸው ለትውልድ ሲያሻግሩ ለቆዩ የኪነ- ጥበብ ባለሙያዎች አስተዳደሩ ልዩ ልዩ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል።

እነዚህ የጥበብ ሰዎች በሀገራዊ ኩራትና በማንነት ግንባታ ውስጥ ያላቸው ሚና ተገቢውን ክብር እንዲያገኝ መታሰቢያዎችን ከመገንባት ጀምሮ የመኖሪያ ቤት ስጦታ ተሰጥቷል።

በቀጣይም ከተማ አስተዳደሩ ለሀገር ውለታ የዋሉ ዜጎችን የመደገፍና የማክበር ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በተለያዩ ጊዜያት አረጋግጧል።

ይህም ለሀገር የሠሩና የደከሙ ዜጎች ምንጊዜም አይረሱም የሚለውን የመንግስት ቁርጠኝነት የሚያንጸባርቅ ነው፡፡

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review