ኤቨርተን ከ ማንችስተር ሲቲ ፡- በዋንጫ ፉክክሩ ትልቅ ትርጉም ያለው ጨዋታ

You are currently viewing ኤቨርተን ከ ማንችስተር ሲቲ ፡- በዋንጫ ፉክክሩ ትልቅ ትርጉም ያለው ጨዋታ

AMN ሚያዝያ 26/ 2018 ዓ.ም

በ35ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ማንችስተር ሲቲ ወደ ሂል ዲኪንሰን ስታዲየም ተጉዞ ኤቨርተንን ይገጥማል፡፡ ለፔፕ ጋርዲዮላው ቡድን ሁለት ጨዋታዎችን ቀድሞ ተጫውቶ የነጥብ ልዩነቱን ወደ ስድስት ያሰፋው አርሰናልን ለመከተል ጨዋታው ወሳኝ ነው፡፡

የምሽቱን ጨዋታ የአርሰናል ደጋፊዎች በጉጉት ይጠብቁታል፡፡ አርሰናል ኒውካስትል ዩናይትድ እና ፉልሃምን በተከታታይ ማሸነፉ ጫናውን ወደ ማንችስተር ሲቲ ገፍቶታል፡፡ ሲቲ ከአርሰናል ጋር በነጥብ ለመስተካከል የግድ ቀሪ ጨዋታዎችን ማሸነፍ አለበት፡፡

የመድፈኞቹ ደጋፊዎች ምንም እንኳን ሲቲ ነጥብ እንዲጥል ቢመኙም ኤቨርተን ይህን ለማድረግ የሚያስችል አቋም ላይ ያለ አይመስልም፡፡ የመርሲሳይዱ ክለብ ባለፉት 10 ዓመታት ከሲቲ ጋር ያለው ክብረወሰን የአርሰናል ደጋፊዎችን ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው፡፡

ማንችስተር ሲቲ ኤቨርተንን በገጠመበት የመጨረሻ ስምንት የሊግ ጨዋታዎች ሁሉንም አሸንፏል፡፡ ኤቨርተን በሊግ ታሪኩ በአንድ ቡድን ይህን ያህል ተከታታይ ጨዋታ በሌላ ክለብ ተሸንፎ አያውቅም፡፡ ኤቨርተን በ2017 ሲቲን 4ለ0 ከረታ በኋላ ባደረጋቸው 17 ጨዋታዎች ድል ለማስመዝገብ አልታደለም፡፡

ከዚህ ውጪ ዴቪድ ሞይስ ከጋርዲዮላ ጋር ያላቸው ደካማ ክብረወሰን የአርሰናል ደጋፊዎች ከኤቨርተን ብዙ እንዳይጠብቁ የሚያደርግ ነው፡፡ ስኮትላንዳዊው አሰልጣኝ ሰንደርላንድን ፣ ዌስትሃም ዩናይትድ እና ኤቨርተንን እየመሩ 15 ጊዜ ፔፕን ገጥመው አንድም ማሸነፍ አልቻሉም፡፡ በ13ቱ ተሸንፈው በሁለቱ ብቻ ነጥብ ተጋርተዋል፡፡ ዛሬስ ምሽት 4 ሰዓት የሚጀምረው ጨዋታ ምላሽ ይሰጠናል፡፡

በጨዋታው በማንችስተር ሲቲ በኩል አማካዩ ሮድሪ መግባቱ አልተረጋገጠም፡፡ ተጫዋቹ አርሰናልን በረቱበት ጨዋታ ጉዳት ገጥሞት ተቀይሮ ከወጣ በኋላ ቡድኑ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ላይ አልተሳተፈም፡፡ ስፔናዊው አማካይ ካልገባ ቲጃኒ ራይንደርስ ፣ ከወራት ጉዳት በኋላ የተመለሰው ማቲዮ ኮቫቺች ፣ ሁለገቡ ኒኮ ኦራይሊ እና ኒኮ ጎንዛሌዝ ቦታውን ለመሸፈን ዝግጁ ናቸው፡፡

ኤቨርተን አጥቂው ቤቶ ይመለስለታል ፤ ተከላካዩ ጃራድ ብራንዝዋይት ግን ከጉዳቱ አላገገመም፡፡

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review