AMN- ሚያዝያ 26/2018 ዓ.ም
የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ተኪ ምርቶችን በማምረት በሀገር ግንባታ ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባዋ ይህንን የገለጹት በከተማ ደረጃ የተዘጋጀውን የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ዓውደ-ርዕይ በይፋ በከፈቱበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ነው።
በዓውደ-ርዕዩ ላይ የቀረቡ የፈጠራ ስራዎችን የጎበኙት ከንቲባዋ ፣ ቀደም ሲል በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ተኪ ምርቶች ለመተካት እየተደረገ ያለው ጥረት ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በመንገድ መሠረተ ልማት ላይ ጥቅም ላይ የሚውሉ ዘመናዊ የመብራት ምርቶችና ሌሎች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ውጤቶች በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች መመረታቸው ለከተማዋ እድገት ትልቅ ግብዓት መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ መቅዳትና ፈጠራ የዓለምን ፈጣን እድገት መቀላቀል እንዳለባት የጠቀሱት ከንቲባ አዳነች፣ መተካት ብቻ ሳይሆን ምርቶቻችንን ወደ ውጭ መላክ ይገባናል ሲሉ አሳስበዋል።
ለዚህም የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በሰሩት ስራ ሳይረኩ ራሳቸውን ለበለጠ ውጤት እንዲያዘጋጁና ከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል።
የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሀገር ግንባታ አካል መሆናቸውንና ሀገር የምትፈልጋቸውን ሰርተው የሚያሳዩ እጆችንና ፈጣሪ አእምሮዎችን በማፍራት ረገድ ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ገልጸዋል።

ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባት አለመቻል ውጤታማነት ተገድቧል ማለት እንዳልሆነ የገለጹት ከንቲባዋ፣ ወጣቶች በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ በመሰልጠን የራሳቸውን ስራ ከመፍጠር ባለፈ ለሀገር ግንባታ የጎላ ድርሻ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችም አዳዲስ ሀሳቦችን የሚያመነጩና ችግር ፈቺ ዜጎችን የማፍራት ኃላፊነታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
ታደሠ ሽፈራው