AMN-ሚያዝያ 27/2018 ዓ.ም
በአውሮፓ ቻምፓየንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ የመልስ ጨዋታ አርሰናል በኤምሬትስ አትሌቲኮ ማድሪድን ያስተናግዳል።
ውጥረት የበዛበት የመጀመሪያው ጨዋታ በዋንዳ ሜትሮፖሊታኖ ተደርጎ 1ለ1 ሲጠናቀቅ ሁለቱም ቡድኖች ግብ ያገኙት በፍፁም ቅጣት ምት ነበር።
አርሰናል የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ፣ ፕሪምየር ሊጉን ደግሞ ከ22 ዓመታት በኋላ ለማሸነፍ አምስት ጨዋታዎች ብቻ ይቀሩታል።
መድፈኞቹ ትናንት ምሽት አንገታቸው ስር የሚተነፍሰው ማንችስተር ሲቲ በኤቨርተን ነጥብ መጣሉ የበለጠ ያነቃቃቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ አሁንም ሽንፈት ያልገጠመው ብቸኛ ክለብ አርሰናል በድምር ውጤት ካሸነፈ በታሪኩ ለሁለተኛ ጊዜ የፍፃሜ ተፋላሚ ይሆናል።
የሰሜን ለንደኑ ክለብ 2005/06 የውድድር ዓመት ለአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ የደረሰበት ብቸኛው ጊዜ ነው። ከ20 ዓመታት በፊት በተደረገው የፍፃሜ ጨዋታ አርሰናል በባርሰሎና 2ለ1 ተሸንፎ ዋንጫ ማጣቱ ይታወሳል።

አትሌቲኮ ማድሪድም የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ አሸንፎ አያውቅም። ሦስት ጊዜ ፍፃሜ ደርሶ አንዱንም በድል መወጣት አልቻለም።
ሁለቱ ክለቦች ከግማሽ ፍፃሜው በፊት በሊግ ምዕራፍ ዛሬ በሚጫወቱበት ኤምሬትስ ስታዲየም ተገናኝተው አርሰናል 4ለ0 ማሸነፉ ይታወሳል።
በዛሬ ጨዋታ በአርሰናል በኩል ማርቲን ኦዴጋርድ እና ካይ ሃቨርትዝ ወደ ስብስቡ እንደሚመለሱ ሚካኤል አርቴታ ተናግሯል።
አትሌቲኮ ማድሪድ በመጀመሪያው ጨዋታ በጉዳት ተቀይሮ የወጣው ሁሊያን አልቫሬዝን በስብስቡ አካቷል።
ምሽት 4 ሰዓት የሚጀምረውን ጨዋታ ጀርመናዊው ዋና ዳኛ ዳኒኤል ሲበርት ይመሩታል።
በሸዋንግዛው ግርማ