AMN-ሚያዝያ 27/2018 ዓ.ም
ለሃገራቸዉ እና ለወገናቸዉ ዉለታ ዉለዋል ወይም የሃገር ባለዉለታ ናቸዉ የሚባሉ ግለሰቦች በአንድ ሀገር ታሪክ፣ ነፃነት፣ ዕድገት እና ስልጣኔ ውስጥ የማይተካ ሚና የተጫወቱ፣ መስዋዕትነት የከፈሉና አሻራቸውን ጥለው ያለፉ ግለሰቦች ናቸዉ፡፡
የሃገር ባለዉለታ የሚባሉት አርበኞች፤ መሪዎች፤ የጥበብ፣ የሳይንስና የትምህርት ሰዎች፤ ደራሲያንና ፈላስፋዎች፤ የስፖርትና የባህል አምባሳደሮች፤ አትሌቶች፤ ድምፃውያንና አርቲስቶች፤ በልማትና በበጎ አድራጎት የተሰማሩ ግለሰቦች፤ ባለሀብቶችና የልማት ሰዎች፤ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና በሌሎች ዘርፎች ለሃገራቸዉ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ናቸዉ፡፡

እነዚህ ግለሰቦች የግል ጥቅምን ሳይሆን የሀገርን ጥቅም ያስቀደሙ፤ ለታሪክ የሚተርፍ በጎ ሥራ የሰሩ፤ ለቀጣዩ ትውልድ አርአያ የሚሆን ተግባር የፈፀሙ ናቸዉ፡፡
የሀገር ባለውለታዎች የሚባሉት ስማቸው በታሪክ መዝገብ የሰፈረ ግለሰቦች ብቻ አይደሉም፡፡ በተለያዩ የስራ ዘርፎች፤ በማህበራዊ ህይወትና መሰል መስኮች በታማኝነትና በቅንነት ሀገራቸውን ያገለገሉ ዜጎች የሃገር ባለዉለታዎች ናቸዉ፡፡

ከሃገር ባለዉለታዎች በተጻራሪ የቆሙ፤ በሃገራቸዉም ሆነ በህዝባቸዉ ዘንድ ክብር ከሚነፈጋቸዉ ግለሰቦች መካከል ደግሞ የራሳቸውን ጥቅም ከሀገር ጥቅም በላይ ያስቀደሙ፤ በሀገር ክህደት ተግባር ላይ የተሰማሩ፤ በሰብአዊ መብት ጥሰት እና በጭካኔ የሚታወቁ ግለሰቦችና መሰል ተግባራትን የፈጸሙ ግለሰቦች ይጠቀሳሉ፡፡
የሀገር ባለውለታዎች መስዋዕትነትን፣ ታማኝነትን እና የህዝብ ጥቅም መቆምን ያስቀደሙ ሲሆኑ እነዚህን እሴቶች የሚጥሱ ግለሰቦች የቱንም ያህል ዝና ቢኖራቸዉ የሀገር ባለውለታ ተብለዉ ላይቆጠሩ ይችላሉ፡፡
የሃገር ባለዉለታዎችን ማሰብና ማክበር በማህበረሰብ የታሪክ ግንባታ እና የትውልድ ቅብብሎሽ ሂደት ዉስጥ ትልቅ ወሳኝ ድርሻ ስላላቸዉ በርካታ ሃገራት የሃገር ባለዉለታዎችን በተለያዩ መንገዶች ያከብራሉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም የሃገር ባለዉለታዎችን ማክበርና ማስታወስ በሃገረ እና ብሔረ መንግስት ግንባታ ዉስጥ ያለዉን ሚና በመገንዘብ በተለያዩ መንገዶች ከመደገፍና ከማበረታታት አልፎ በመዲናዋ ዉስጥ የመታሰቢያ ሃዉልት እንዲቆምላቸዉ አድርጓል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ