በአዲስ አበባ ድህነትን በሥራ፣ ጥገኝነትን በምርታማነት የመተካት ጉዞው አበረታች ውጤት እያመጣ ነው

You are currently viewing በአዲስ አበባ ድህነትን በሥራ፣ ጥገኝነትን በምርታማነት የመተካት ጉዞው አበረታች ውጤት እያመጣ ነው

AMN- ሚያዝያ 28/2018 ዓ.ም

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ ከተደረጉት አምስቱ የ“ዜሮ ግቦች” መካከል አንዱና ዋነኛው “ተረጂነትን እና ልመናን ዜሮ ማድረግ” ነው፡፡

በከተማዋ እየተተገበሩ ያሉ የሰው ተኮር ፕሮጀክቶች ድህነትን በሥራ፤ ጥገኝነትን በምርታማነት በመተካት አበረታች ውጤት በማስመዝገብ ላይ ይገኛሉ፡፡

ቀደም ሲል “በነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል” አማካኝነት ከአስከፊ ህይወት የወጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ዛሬ ላይ ራሳቸውን ከመቻል ባለፈ ለበርካቶች የሥራ እድል ፈጥረዋል።

እንዲሁም ከተማ አስተዳደሩ በምግብ ዋስትና እና ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም 15 ሺህ 492 ተጠቃሚዎችን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በማሸጋገር አስመርቋል።

በተጨማሪም ባሳለፍነው ዓመት በምግብ ዋስትና (ሴፍቲኔት) ፕሮግራም ታቅፈው ሲሰሩ ለነበሩ የከተማዋ ነዋሪዎችን ወደ 976 አንቀሳቃሾች እና በ292 ኢንተርፕራይዞች እንዲደራጁ በማድረግ በአዲስ ከተማ፣ በአቃቂ ቃሊቲ፣ በየካ እና በቂርቆስ ክፍለ ከተሞች፣ ባለ አራት ወለል የማምረቻ እና መሸጫ ህንፃዎችን አስረክቧል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻልና ምርታማነትን ለማሳደግ የጀመረው ይህ የተቀናጀ ጥረት ዛሬ ላይ ለሺዎች የሥራ ዕድልና ተስፋ ሆኗል።

አሁንም ከተማ አስተዳደሩ የነዋሪዎችን ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የማያቋርጥ ሥራ እየሰራ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ብቻ ከ10 ሺህ በላይ የሥራ ቦታዎችንና ሼዶችን በመገንባት አስተላልፏል፡፡

በዛሬው ዕለትም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በመዲናዋ በ11ዱም ክፍለ ከተሞች ለሚገኙ ለ1 ሺህ 278 ኢንተርፕራይዞች እና ለ3 ሺህ 889 አንቀሳቃሾች ሼዶችና የመስሪያ ቦታዎች አስተላልፈዋል።

እነዚህ ኢንተርፕራይዞችና አንቀሳቃሾች የሥራ እድል እንዲፈጠርላቸው እንደየፍላጐታቸው የተደራጁ እና የሰለጠኑ ሲሆን፣ በ3 ወራት ውስጥ ተጠናቀው የተረከቧቸው ሼዶችና የመስሪያ ቦታዎች በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ እድልን በመፍጠር ምርታማነትን ይጨምራሉ፡፡

በርክክብ ሥነ ስርዓቱም ወቅት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ “የሚሰሩ እጆችን እናበረታታለን! ያሉ ሲሆን፣ በጋራ ለማደግ፣ በጋራ ለመለወጥና ለሀገር እድገት የበኩላችሁን አስተዋፅዖ ማበርከት እንድትችሉ አደራ እላለሁ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በአዲስ አበባ የሚሰሩ እጆችን በማብቃትና ምቹ የሥራ አካባቢን በመፍጠር ረገድ የተጀመሩት መሰል ተግባራት የመዲናዋን ነዋሪዎች ወደ ብልጽግና እያሸጋገረ መሆኑን ያሳያል።

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review