16ኛው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት አውደ-ርዕይና የፈጠራ ሥራዎች ውድድር ተጠናቀቀ

You are currently viewing 16ኛው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት አውደ-ርዕይና የፈጠራ ሥራዎች ውድድር ተጠናቀቀ

AMN- ሚያዝያ 28/2018 ዓ.ም

ላለፉት ቀናት በአራዳ ፓርክ “የቴክኖሎጂ ልህቀት ለሀገር ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ ሲካሄድ የቆየው 16ኛው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት አውደ-ርዕይና የፈጠራ ሥራዎች ውድድር በደማቅ ሥነ-ስርዓት ተጠናቋል።

በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ በምክትል ከንቲባ መዕረግ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ፤ የቴክኖሎጂ ታሪክ የኢኮኖሚ ልማት ታሪክ መሆኑን በጥልቀት በመተንተን፣ ባለፉት ቀናት የቀረቡት የፈጠራ ሥራዎች የሀገሪቱን የልማት ተስፋና ተጨባጭ እንቅስቃሴ የሚያመላክቱ ናቸው ብለዋል።

መንግስት የክህሎት መር የሥራ ስምሪትን እንደ ዋነኛ ፖሊሲ በመከተሉ፣ ወጣቶች ያላቸውን እምቅ አቅም በተግባር እንዲያሳዩና በ21ኛው ክፍለ ዘመን ራሳቸውን በእውቀት፣ በክህሎትና በሥነ-ምግባር በማነጽ ለሀገራቸው ብልጽግና እንዲተጉ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አብራርተዋል።

አክለውም፣ ወጣቶች የሥራን ክብር በመረዳትና ዲጂታል ክህሎታቸውን በማሳደግ የሀገር ግንባታ አካል እንዲሆኑና የጀመሩትን የፈጠራ ሥራ ወደ ቢዝነስ በመቀየር ራሳቸውን እንዲያዘጋጁም አደራ ብለዋል።

የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚደቅሳ ከበደ በበኩላቸው፣ የዘንድሮው አውደ-ርዕይ ቴክኖሎጂዎችን ለዕይታ ብቻ ከማቅረብ ባለፈ፣ በቀጥታ ወደ ፋብሪኬሽን ኢንጂነሪንግ በማሸጋገር ለተጠቃሚው ተደራሽ እንዲሆኑ የሚያስችል አዲስ ስትራቴጂ የተተገበረበት መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የውጭ ምንዛሬን የሚያድኑ ተኪ ምርቶችን ማምረት እንደሚችሉ በተግባር ያረጋገጡበት መድረክ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዕለቱ በቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ በዲጂታል አይሲቲ ቴክኖሎጂዎች ፈጠራ፣ በፋሽን ዲዛይን፣ በተግባራዊ ጥናትና ምርምር ውድድር ከፍተኛ ውጤት እንዲሁም በስፖርት ውድድር አሸናፊ በመሆን በደረጃ ለወጡ ተወዳዳሪዎች እውቅና እና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።

በመድረኩ የተጀመረው የቴክኖሎጂ ሽግግርና የምርት መተካት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መገለጹን የቢሮው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review