አዲስ አበባን ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭ መዲና ያደረጋት ምንድነዉ?

You are currently viewing አዲስ አበባን ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭ መዲና ያደረጋት ምንድነዉ?

AMN- ሚያዝያ 29/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን ከፍ ወደ አለ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽነት በመቀየር የኮንፈረንስ ቱሪዝም መናገሻነቷን እያሰፋች ትገኛለች።

እ.ኤ.አ በ2026 በመዲናዋ የሚካሄዱ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ኹነቶች ከተማዋን በአፍሪካ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭ መዳረሻ እየሆነች መምጣቷን የሚያመላክት ነው።

ኮንፈረንስ አለርት የተሰኘው የተረጋገጡ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ፣ ኮንፈረንሶችንና ሴሚናሮችን በመከታተል ጥቆማ የሚሰጠው ድረ-ገጽ በመጪዎቹ ወራት እ.ኤ.አ 2026 መጠናቀቂያ ድረስ 200 የሚጠጉ ኮንፈረንሶች በአዲስ አበባ እንደሚካሄዱ አስቀምጧል።

ይካሄዳሉ ተብለው የሚጠበቁት ኮንፈረንሶች በቢዝነስ ፣ ኢንጂነሪንግ ፣ ቴክኖሎጂ ፣ ህክምና ፣ ትምህርት ፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሠራሽ አስተውሎት) ፣ ሶሲዮሎጂ ፣ ባንክ ፣ ወጣቶች ፣ ቱሪዝም እና በሕግ ዘርፎች የተከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ከተሜነትን እንድትቀላቀል እያስቻሏት ነው።

እንደ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ፣ እጅግ ዘመናዊው የሳይንስ ሙዚየም ፣ የአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል የመሳሰሉት ከተማዋ ከዚህ ቀደም የነበረባትን የስብሰባ አዳራሾች እጥረት እንድትቀርፍ ካስቻሏት ይጠቀሳሉ።

በቅርቡ የተመረቁት እንደ አርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት አዳዲስ ላቦራቶሪዎች ፣ አዲስ አበባን ለሳይንሳዊ ኮንፈረንስ ተመራጭ እንድትሆን እንደሚያስችላት ይጠበቃል።

የአዲስ ስፖርት ፓርክ በቅርቡ መመረቅ ለስፖርታዊ ኮንፈረንሶች ፣ ለኤግዚቢሽኖች እና ውድድሮች አዲስ በር የሚከፍት ነው።

የኮንፈረንስ ቱሪዝም ከተለመደው የመዝናኛ ቱሪዝም በበለጠ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ ዘርፍ ነው። አንድ ለስብሰባ የመጣ እንግዳ ከመዝናኛ ቱሪስት በአማካይ እስከ ሦስት እጥፍ የሚበልጥ ወጪ እንደሚያወጣ ጥናቶች ያሳያሉ።

የኮንፈረንስ ቱሪዝም ከሆቴሎች ባለፈ ለትራንስፖርት፣ ለባህል አልባሳትና ለምግብ ዘርፍ ትልቅ ገቢ ያስገኛል። አንድ እንግዳ ስብሰባውን አጠናቆ በሚያርፍባቸው ጊዜያት እንደ አንድነት ፣ ወዳጅነት እና አራዳ ፓርኮች ያሉ አረንጓዴ ስፍራዎችን ሲጎበኝ ለከተማዋ ተጨማሪ ገቢን ይፈጥራል።

የመዲናዋ የኮሪደር ልማት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚጠቀሱ ከተሞችን የሚመስል የእግረኛ መንገድና የውበት ደረጃ ስላጎናጸፋት ፣ እንግዶች በከተማዋ በነፃነት እንዲንቀሳቀሱና ግብይት እንዲፈጽሙ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው።

አዲስ አበባ አሁን ላይ ያላት ዝግጁነት ከወትሮው የተለየ ነው። ዘመናዊ የመሰብሰቢያ ማዕከላት፣ ታሪካዊ ሙዚየሞች እና የተፈጥሮ መናፈሻዎች ተደምረው ከተማዋን የአፍሪካ የኮንፈረንስ መናገሻ የሚያደርጋት ነው። በቀጣይ የሚካሄዱት ሁነቶችም ይህንን እውነታ ይበልጥ የሚያረጋግጡ ይሆናል።

በታደሠ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review