አዲስ አበባ የአፍሪካ የዲጂታል ልብ ትርታ

You are currently viewing አዲስ አበባ የአፍሪካ የዲጂታል ልብ ትርታ

AMN- ሚያዝያ 29/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የአፍሪካን የዲጂታል ትረካ ለመቀየር ታሪካዊ እርምጃ ወስዳለች።

በአዲስ አበባ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው የመጀመሪያው የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ፣ አገሪቱ በአህጉራዊ የዲጂታል ዲፕሎማሲ ያላትን ሚና ከፍ ከማድረጉም በላይ ለዓለም አቀፍ ገጽታ ግንባታ አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል፡፡

ይህ ታላቅ ጉባኤ ለኢትዮጵያ መልካም ገጽታ ግንባታ በርካታ አንድምታዎች ያሉት ሲሆን የሚከተሉትን በአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ ይህ ጉባኤ አህጉራዊ ጉዳዮች በአፍሪካዊያን እይታና ድምፅ እንዲተረኩ መድረክ ይፈጥራል።

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሏቸው ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በአዲስ አበባ መገኘታቸው፣ የአገሪቱን እውነተኛ ገጽታ ለዓለም በቀጥታ እንዲያስተላልፉ በማድረግ የዲጂታል ዲፕሎማሲ ስኬት ሆኖ ይመዘገባል፡፡

የከተማዋ የኮሪደር ልማት፣ የታደሱ ታሪካዊ ስፍራዎች እና እንደ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በተፅዕኖ ፈጣሪዎቹ ካሜራ አማካኝነት ለዓለም ተደራሽ ይሆናል።

ይህ ምስላዊ ትረካ፣ የኢትዮጵያን ዘመናዊና ማራኪ የቱሪስት መዳረሻ በማስተዋወቅ ረገድ ከማንኛውም የሚከፈልበት ማስታወቂያ የላቀ ውጤት ያመጣል፡፡

መድረኩ አዲስ አበባ ግዙፍ አህጉራዊ ዝግጅቶችን የማስተናገድ ብቃትና አስተማማኝ ሰላም እንዳላት ማረጋገጫ በመሆኑ፣ የውጭ አገራት ዜጎች በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ በነፃነት በመንቀሳቀስ ከተማዋን መጎብኘት እንደሚችሉ ማሳያ ይሆናል፡፡

ጉባኤው ኢትዮጵያ ለቴክኖሎጂና ለፈጠራ የሰጠችውን ትኩረት ለዓለም ያሳያል። እንደ 5 ሚሊዮን ኮደሮች እና የዲጂታል መታወቂያ ያሉ ሀገራዊ ተነሳሽነቶች ከጉባኤው ዓላማ ጋር ተዳምረው፣ አገሪቱ የአፍሪካ የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ማዕከል ለመሆን ያላትን ቁርጠኝነት ያመላክታል።

ባጠቃላይ ይህ ጉባኤ በዲጂታሉ ዓለም የምትገነባውን የኢትዮጵያን ገጽታ፣ በአካል ከሚሰሩ የልማት ስራዎች ጋር ተዳምሮ አገሪቱ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሰሚነት ከፍ ያደርጋል።

ተፅዕኖ ፈጣሪዎቹ የሚፈጥሩት ይዘት በኢንተርኔት ዓለም ለረጅም ጊዜ የሚቆይ በመሆኑ፣ በውጤቱም ቀጣይነት ያለው ብሄራዊ ፋይዳ ይኖረዋል።

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review