የ“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው – የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ

You are currently viewing የ“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው – የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ

AMN – ሚያዝያ 29/2018 ዓ.ም

የ“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ እንደ ሀገር እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።

ፕሬዝዳንቱ በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ያለውን 4ኛውን የ“ኢትዮጵያ ታምርት” ኤክስፖ በጎበኙበት ወቅት እንደተናገሩት፣ ንቅናቄው የሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ከፍ በማድረግ፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በማሳደግና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማሳለጥ ረገድ ተጨባጭ ውጤቶች የታዩበት ሆኗል።

በኤክስፖው የቀረቡ ምርቶች በሀገር ልጆች የተመረቱ መሆናቸውን የተመለከቱት ፕሬዝዳንቱ፣ የማምረት አቅሙ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ላቀ ደረጃ መሸጋገሩ እጅግ የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

እነዚህን በሀገር ውስጥ በከፍተኛ ጥራት የሚመረቱ ምርቶች ለዓለም ገበያ ለማስተዋወቅም የኢትዮጵያ ቆንፅላዎችና የዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖች በቆራጥነት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተለይም ሚሲዮኖቹ ምርቶቹን በአምባሳደርነት የማስተዋወቅና ሰፊ የገበያ ዕድሎችን የመፍጠር ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

ባለፉት ቀናት ሲካሄድ የቆየውና በርካታ አምራቾች የተሳተፉበት ይህ 4ኛው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ፣ እስከ ነገ ሚያዝያ 30/2018 ዓ.ም ድረስ ለጎብኚዎች ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ከኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የተላከ መረጃ ያመለክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review