ለውጡን ተከትሎ በአዲስ አበባ የተገነቡ የጤና ተቋማት ባለፉት መቶ ዓመታት ከነበረው በሁለት እጥፍ ዕድገት አሳይቷል

You are currently viewing ለውጡን ተከትሎ በአዲስ አበባ የተገነቡ የጤና ተቋማት ባለፉት መቶ ዓመታት ከነበረው በሁለት እጥፍ ዕድገት አሳይቷል

AMN – ግንቦት 03/2018 ዓ.ም

የሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡ የጤና ተቋማት፣ ከተማዋ ባለፉት መቶ ዓመታት ካስመዘገበችው አጠቃላይ ቁጥር ጋር ሲነፃፀር የሁለት እጥፍ ዕድገት ማሳየታቸው ተገለጸ።

የከተማ አስተዳደሩ የነዋሪዎችን ጤና ለማረጋገጥ ባከናወናቸው አበረታች ተግባራት በርካታ አዳዲስና ዘመናዊ ሆስፒታሎች ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ፤ ባለፉት መቶ ዓመታት ማለትም እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ በከተማ አስተዳደሩ ሥር የሚተዳደሩ ሆስፒታሎች የነበራቸው አጠቃላይ የአልጋ ብዛት 1 ሺህ 384 ብቻ ነበር።

በአሁኑ ወቅት ግን 2 ሺህ 811 አዳዲስና ዘመናዊ አልጋዎችን በመጨመር በከተማዋ የሚገኘውን የሕክምና አልጋ ቁጥር ወደ 4 ሺህ 195 ማድረስ ተችሏል።

በከተማዋ አዲስ ከተገነቡት ዘመናዊ የጤና ተቋማት መካከል የአበበች ጎበና ሆስፒታል በዘመናዊ መልክ ተገንብቶ ለእናቶችና ሕፃናት ልዩ የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጓል።

በተመሳሳይ 500 አልጋዎች የሚይዘው ቤቴል ማይንዳ ሆስፒታል በአሁኑ ወቅት ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎች እየገቡለት የሚገኝ ሲሆን፣ በተያዘው ግንቦት ወርም ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ይገባል።

ሌላኛው ባለ 500 አልጋው ንፋስ ስልክ ላፍቶ ሆስፒታል ደግሞ ግንባታው ተጠናቆ ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎችን የማሟላትና የሰው ኃይል የማደራጀት ሥራ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ከአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ አገልግሎት መጀመር የሚያስችለው ዝግጅት እየተደረገ ነው።

ከተማ አስተዳደሩ ከሚያስተዳድራቸው የጤና ተቋማት መካከል በከተማዋ ትልቁ ሆስፒታል የሆነውና 577 አልጋዎችን የያዘው የገላን ትራውማ ሴንተር የድንገተኛ ሕክምና ሆስፒታልም በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ወደ ሥራ እንዲገባ ታቅዶ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።

ከአዳዲስ ግንባታዎች በተጨማሪ ነባር ሆስፒታሎችን በከፍተኛ ጥራት የማደስና የማስፋፋት ሥራዎች ተከናውነዋል።

በዚህም መሠረት በዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል ሁለት ተጨማሪ አዳዲስ ሕንፃዎች የተገነቡ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ባለ አምስት ወለል ዘመናዊ የአይን ሕክምና እና የኩላሊት እጥበት ማዕከል ነው።

ይህ ማዕከል በአሁኑ ወቅት ከ200 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ዘወትር የኩላሊት እጥበት አገልግሎትን በነፃ እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን የአልጋ ቁጥሩም በዚያው ልክ እንዲጨምር ተደርጓል።

የራስ ደስታ ዳምጦ መታሰቢያ ሆስፒታልም የላቀ የሕክምና ማዕከል እንዲኖረው ለማድረግ ባለ ስድስት ወለል አዲስ ሕንፃ እየተገነባለት ይገኛል።

ይህ ግንባታ ተቋሙ የነበረውን የታካሚዎች ማቆያና ማከሚያ ክፍሎች በእጥፍ የሚያሳድግ ሲሆን፣ 320 ተጨማሪ አልጋዎችን ይይዛል።

በአሁኑ ወቅት የኦክስጅን ማምረቻ መሣሪያ እየተገጠመለት የሚገኘው ይህ ተቋም በቅርቡ አገልግሎት መስጠት የጀምራል።

በሌላ በኩል በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ባለፈው ዓመት 64 አልጋዎች ያሉት የመጀመሪያው የተቀናጀ የሕፃናት አንጎልና ሕብለ-ሰረሰር ቀዶ ሕክምና የልህቀት ማዕከል ተገንብቶ መመረቁ ይታወሳል።

በተጨማሪም በተያዘው ዓመት የተመረቀው ባለ 10 ወለል ሕንፃ 320 አልጋዎች ያሉት ሲሆን፣ የሆስፒታሉን የነበረውን የአልጋ ቁጥር በእጥፍ አሳድጎታል።

በከተማዋ ለመጀመሪያ ጊዜ በሆስፒታል ደረጃ አዳዲስ ዘጠኝ የጤና ጣቢያዎች ተገንብተው እስከ ቀዶ ጥገና ድረስ ያሉ የሕክምና አገልግሎቶችን መስጠት የጀመሩ ሲሆን፣ 40 ነባር የጤና ጣቢያዎች ደግሞ በማስፋፊያ መልክ በከፍተኛ ጥራት ተገንብተው አገልግሎታቸውን አሳድገዋል።

በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራት ከማረጋገጥ አንጻር የተከናወኑት ተግባራት፤ ከተማዋ ባለፉት መቶ ዓመታት እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ ከነበራት አጠቃላይ አቅም ጋር ሲነጻጸር ከሁለት እጥፍ በላይ ዕድገት ማሳየቱን ያረጋገጡ ሆነዋል።

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review