AMN- ግንቦት 3/2018 ዓ.ም
የትላንቱ የዌስትሃም እና አርሰናል ጨዋታ በ2025/26 የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ላይ ከወቅቱ እጅግ አነጋጋሪ ጨዋታዎች አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል። ጨዋታው ሊያንድሮ ትሮሳርድ 83ኛ ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል 1-0 በአርሰናል አሸናፊነት ቢያበቃም፣ ሁሉም እያነጋገረ ያለው ግን በ90+4 ደቂቃ የተከሰተውን የVAR ውሳኔ ነው።
አርሰናል በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ጨዋታውን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ ነበር። የድክላን ራይስ ቅጣት ምት፣ የሪካርዶ ካላፊዮሪ የአየር ኳሶች እና የዴቪድ ራያ የጀርባ ግንብ የዌስትሃምን ግፊት አስቀድሞ አዳክሞት ነበር። ነገር ግን ቤን ዋይት በጉዳት ከወጣ በኋላ የሚኬል አርተታ የቦታ ለውጥ ጨዋታውን አስቸጋሪ አደረገው።
ዴክላን ራይስን ወደ ቀኝ ተከላካይ ማውረድ የመሀል ሜዳውን አዳከመ፣ ይህም ዌስትሃም በቀስታ ወደ ጨዋታው እንዲመለስ አደረገ። በሁለተኛው አጋማሽ አርሰናል ኳስ ይዞታን ቢቆጣጠርም ግልጽ ዕድሎች ግን እየቀነሱ መጡ። ይህ የጨዋታውን ውጥረት ከፍ አደረገው።
90+4 ላይ ዌስትሃም ከማዐዘን ምት ያገኘው ኳስ በሳጥኑ ውስጥ በተፈጠረ ትርምስ ኳሱ ወደ ካሉም ዊልሰን ደረሰ፣ እሱም ኳሱን ወደ መረብ ላከው። የለንደን ስታዲየም በደስታ ፈነዳ፤ የዌስትሃም ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች እኩል ነጥብ አግኝተዋል ብለው አመኑ።

ነገር ግን VAR ጨዋታውን አቆመ። ዳኛው ኪሪስ ካቫና 17 ጊዜ ድጋሚ ቪዲዮውን እንዳየ ዘ ጋርዲያን ዛሬ ይዞት በወጣው መረጃ አስነብቧል። መጨረሻ ላይ ውሳኔው “በዴቪድ ራያ ላይ ጥፋት ተፈጽሟል” ተብሎ ጎሉ ተሻረ። ይህ የእግር ኳስ ዓለምን ለሁለት ከፍሎታል።
ዘ ሰን ይዞት በወጣው መረጃ ፣ አንዳንድ ተንታኞች የዌስትሃም ተጫዋቾች ራያን በእጅ እና ማሊያውን በመያዛቸው መዝለል እንዳይችል አድርገውታል ይላሉ። በተለይ የቀድሞ ዳኛዎች “ይህ በህግ መሠረት ጥፋት ነው” ሲሉ ተከራክረዋል። የአርቴታ አስተያየትም ይህንን ያጠናክራል። “ዳኞቹ ድፍረት አሳይተዋል” ሲል ውሳኔውን ደግፎታል።
ይህ ዉሳኔ “የተመረጠ ፍትህ ነው” ያሉም አልጠፉም፡፡ ችግሩ ውሳኔው ብቻ አይደለም ይላሉ ፤ “የወጥነት” ወይም የተመሳሳይ ውሳኔ አለመኖር ነው ችግሩ የሚሉ በርካታ ናቸው።
የዌስትሃሙ የፊት መስመር ተጫዋች ጃሮድ ቦውን “በኮርነር ጊዜ መገፋፋትና መያያዝ የፕሪሚየር ሊግ እግር ኳስ አካል ሆኗል ፤ ዛሬ ግን በድንገት ፋውል ሆነ” ሲል ቅሬታ አቅርቧል።

ሌሎች እግር ኳስ ተንታኞች “አርሰናል ራሱ በዚህ ዓይነት የግብ ጠባቂ ጫና ጎሎች ሲያስቆጥር ብዙ ጊዜ አልተቀጣም” በማለት የሁለት ዓይነት መለኪያ እንዳለ አንስተዋል።
ይህ ውሳኔ በሁለት የተለያዩ ክለቦች ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ አለው፡፡ የመጀመሪያው ፤ አርሰናል ከማንችስተር ሲቲ በ 5 ነጥብ ርቆ የዋንጫ እድሉን እንያጠናክር ሲያደርግ ዌስትሃም ደግሞ ወደ ወራጅ ቀጠናው በእጅጉ አስጠግቷል።
VAR የተፈጠረው ፍትህን ለማምጣት ነበር ፣ ነገር ግን እንደ ትላንቱ ጨዋታ ሲሆን የደጋፊዎችን የጎል ደስታ ለ4 ደቂቃ ማቆም፣ ከዚያም አከራካሪ ውሳኔ መስጠት ቴክኖሎጂው ራሱ የጨዋታውን ስሜት እየቀየረ መሆኑን ያሳያል ሲሉ በርካታ የእግር ኳስ ወዳዶች ይገልጻሉ።
በብዙዎች ዓይን የትላንቱ ጨዋታ የአርሰናል 1-0 ድል ብቻ አልነበረም ፤ የዘመናዊ እግር ኳስ ከቴክኖሎጂ ጋር ያለውን ውስብስብ ግንኙነት ያጋለጠ 90 ደቂቃም ነበር። VAR ፍትህን ለማረጋገጥ የተፈጠረ ቢሆንም፣ እንደዚህ ያሉ አከራካሪ ውሳኔዎች ግን “ፍትህ በእርግጥ እየተሰጠ ነውን? ወይስ የጨዋታውን ስሜትና ድንቅ ጊዜያት እያደበዘዘ ነው?” የሚለውን ጥያቄ እያጠናከሩት ይገኛሉ።

የዌስትሃም ደጋፊዎች የተነጠቁትን እኩል ነጥብ ሲያስቡ ህመም ይሰማቸዋል ፤ የአርሰናል ደጋፊዎች ደግሞ ይህን እንደ ዋንጫ ጉዞአቸው ወሳኝ ቅጽበት ያዩታል። ግን ከሁሉ በላይ ትላንቱ ያሳየው ፣ በዘመናዊ እግር ኳስ ውስጥ ጨዋታዎች ከረዳት ዳኞችና ተጫዋቾች በላይ ፣ በስክሪን ፊት ባሉ ውሳኔዎችም እየተወሰኑ መሆናቸውን ነው።
በቶለሳ መብራቴ