AMN- ሰኔ 16/2018 ዓ.ም
ቻተም ሃውስ የተሰኘው ዓለም አቀፍ ተቋም በለንደን ባዘጋጀውና “በተከፋፈለ ጂኦ-ፖለቲካዊ ሁኔታ ውስጥ የኮፕ ጉባኤዎችን አስፈላጊነት ማጉላት” በሚል ርዕስ በተካሄደው የአየር ንብረት ሳምንት የውይይት መድረክ ላይ፣ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ32 ተሰያሚ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ፣ የኮፕ30 ፕሬዚዳንት አንድሬ ኮሬያ ከብራዚል እንዲሁም የኮፕ31ን የወከሉት የቱርክ የአካባቢ፣ የከተማ ልማት እና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር በተገኙበት ውይይቱ ተካሂዷል።
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ጥበቃ ረገድ ያላትን ጠንካራ ርዕይ እና አመርቂ አፈጻጸም ያነሱት ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ፣ በተለይም ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ በፖሊሲ ተደግፈው ተግባራዊ የተደረጉ አፈጻጸሞችን አጽንኦት ሰጥተው አብራርተዋል።

ዶክተር ጌዲዮን አክለውም፣ ኢትዮጵያ በምታዘጋጀው የኮፕ32 ቀዳሚ ተግባራት፣ በቱርክዬና አውስትራሊያ በጋራ ከሚዘጋጀው የኮፕ31 የተገኙ ውጤቶች በመነሳት፣ ቀጣይነትን ማረጋገጥ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
ይህ አካሄድ ደግሞ፣ ከእኛ በፊት ከነበሩት ጋር በቅንጅት በመስራት፣ የጋራ ተግባራትን ማጠናከርና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ሂደት ላይ ያለውን ተስፋ መልሶ ማቀጣጠል የሚለውን የ“መደመር” መርህ እንደሚያንጸባርቅ አፅንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።