የዓለም ዋንጫ የ32 ሀገራት ማጣሪያ የመጨረሻ ጨዋታዎች

You are currently viewing የዓለም ዋንጫ የ32 ሀገራት ማጣሪያ የመጨረሻ ጨዋታዎች

AMN-ሰኔ 26/2018 ዓ.ም

የ23ኛው የዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ዛሬ በሚከናወኑ ሦስት ጨዋታዎች ይጠናቀቃል።

እስካሁን በተደረጉ ጨዋታዎች 13 ሀገራት 16 ብሔራዊ ቡድኖች ወደ ሚፋለሙበት ጥሎ ማለፍ የሚሸጋገሩ ሲሆን፤ ዛሬ ሦስት ሀገራት ቆይታቸውን ያራዝማሉ።

አውስትራሊያ ከ ግብፅ

አውስትራሊያ እና ግብፅ ተመጣጣኝ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ምድብ ሰባትን ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ ያጠናቀቀችው ግብፅ ታሪካዊ የዓለም ዋንጫ እያሳለፈች ትገኛለች።

ከአፍሪካ ቀዳሚዋ የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ የሆነችው ግብፅ ምድቧን አልፋ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ስታደርግ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ለግብፅ መጥፎ ዜና ሞሐመድ ሳላህ መግባቱ አለመረጋገጡ ሲሆን፤ የ34 ዓመቱ ኮከብ የጡንቻ ጉዳት እንደገጠመው ተነግሯል።

ሰባተኛ የዓለም ዋንጫዋን እየተሳተፈች የምትገኘው አውስትራሊያ ወደ ጥሎ ማለፍ ዙር ስትገባ የዘንድሮው ለሦስተኛ ጊዜ ነው።

አሜሪካ በነበረችበት ምድብ አራት ነጥብ በመያዝ ሁለተኛ ያጠናቀቀችው አውስትራሊያ በመከላከሉ ይበልጥ ተዋቶላታል።

ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫ ሲገናኙ በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ጨዋታው ምሽት 3፡00 ላይ በዳላስ ስታዲየም የሚከናወን ይሆናል።

አርጀንቲና ከኬፕ ቨርድ

የወቅቱ የዓለም ዋንጫ ባለቤት አርጀንቲና በርካቶችን እያስደመመች የምትገኘው ኬፕ ቨርድን ትገጥማለች።

ጨዋታው በወረቀት ላይ ፍፁም ለንፅፅር የማይቀርቡ ሀገራት የሚያካሂዱት ነው። ቢሆንም ግን ኬፕ ቨርድ በምድብ ጨዋታዎቿ ከስፔን እና ኡራጓይ ጋር ተፋልማ ነጥብ ከተጋራች በኋላ ዝቅተኛ ግምት እንዳይሰጣት አድርጋለች።

ሦስቱንም ምድብ ጨዋታዎች ያሸነፈችው አርጀንቲና አሁንም በሊዮኔል ሜሲ ላይ ጥገኛ ናት። ቡድኑ ካስቆጠራቸው ስምንት ግቦች ስድስቱ በሜሲ ስም የተመዘገቡ ናቸው። 39 ዓመት ሞልቶትም አስተዋፅኦ ያልቀነሰው ሜሲ በዛሬውም ጨዋታ ይጠበቃል።

ኬፕ ቨርድ እንደ ቡድን ያሳየችውን የመከላከል ብቃት ዛሬም ልትደግመው ትችላለች። በሚያሚ ስታዲየም ለሊት 8፡00 የሚከናወነው ጨዋታ ሁለቱን ሀገራት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያገናኝ ይሆናል።

ኮሎምቢያ ከ ጋና

በካንሳስ ሲቲ ስታዲየም ሚደረገው የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ለሊት 10፡30 ይጀምራል። ኮሎምቢያ ፖርቹጋል የነበረችበት ምድብ 11ን በበላይነት አጠናቃለች።

ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ጋና በአንፃሩ በምድብ 12 እንግሊዝ እና ክሮሺያን ተከትላ ነው ያለፈችው።

ሁለቱ ሀገራት ከዚህ ቀደም በየትኛውም ውድድር ተገናኝተው አያውቁም።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review