AMN- ግንቦት 3/2018 ዓ.ም
በኢትዮጵያ እና ቻይና መካከል ያለው በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ሀገራቱን አስተማማኝ የልማት አጋሮች እንዳደረጋቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከቻይና ሕዝብ ብሔራዊ ኮንግረንስ የልዑክ ቡድን አባላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ ኢትዮጵያ እና ቻይና እ.አ.አ ከ2023 ጀምሮ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በሁኔታዎች ወደማይለዋወጥ ስትራቴጂካዊ አጋርነት አሳድገዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት በዓለም አቀፍ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ እርስ በርስ በመደጋገፍ ግማሽ ክፍለ ዘመን የተሻገረ መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሥርተዋል፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የአንድ ቻይና ፖሊሲን ትደግፋለች፡፡

የአፍሪካ ሀገራትን ተጠቃሚ በሚያደርገው የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ዝርጋታን ጨምሮ በተለያዩ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ተጠቃሚ መሆኗን ገልጸዋል፡፡
ቻይና የኢትዮጵያ አስተማማኝ አጋር መሆኗን ገልጸው፤ የኢትዮጵያ የግብርና፣ ማዕድን፣ የጨርቃጨርቅና ሌሎች ምርቶች ቀዳሚ ተቀባይ ሀገር ሆናለች ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የቻይና ኩባንያዎች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት አምስት ቢሊየን ዶላር መድረሱን በመጥቀስ፤ ከሁለት ሺህ በሚልቁ ፕሮጀክቶች ከ560 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ገልጸዋል፡፡
በቻይና-አፍሪካ ማዕቀፍ የሁለቱ ሀገራት ትብብር ጠንካራ መሰረት ያለው መሆኑን በመግለጽ፤ ኢትዮጵያ ለውጭ ኢንቨስትመንት ትርጉም ያለው የቢዝነስ ከባቢ ፈጥራለች ብለዋል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ትብብር እያደገ መምጣቱን በማንሳት፤ በበርካታ ዘርፎች የትብብር ስምምነቶችን በመፈራረም በተግባር የሚገለጽ ውጤት ማስመዝገባቸውን አንስተዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት የሕግ አውጪዎች የውይይትና የልምድ ልውውጥ መድረክ የሕዝብ ለሕዝብና የተቋማት ትብብርን ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን እምቅ የባህልና የቅርስ ሀብት ለቱሪዝም ልማት ማዋል እንዲችሉ በትብብር እንሰራለን ብለዋል፡፡
የቻይና ብሔራዊ ኮንግረንስ የትምህርት፣ ሳይንስ፣ ባህልና የማህበረሰብ ጤና ኮሚቴ ሊቀ መንበርና የልዑኩ መሪ ሉ ሹጋንግ ወደ ኢትዮጵያና ውቧ አዲስ አበባ ለጉብኝት በመምጣታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ እና ቻይና በባህል፣ ቅርስና በቱሪዝም ሀብት የታደሉ ሀገራት መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የሁለቱ ሀገራት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እየተጠናከረ መጥቷል ነው ያሉት፡፡
በሁለቱ ሀገራት ምክር ቤቶች መካከል የሚደረገው እውነተኛ ትብብር በማንኛውም ጊዜ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ እና ቻይና የረጅም ጊዜ ትብብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ አመራር ሰጪነት በሁኔታዎች ወደማይለዋወጥ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ማደጉን አውስተዋል።
ሀገራቱ በዓለም አቀፍ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ እርስ በርስ እንደሚደጋገፉ በማንሳት፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸው አድማሱን እያሰፋ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
ቻይና የተፈረሙ ስምምነቶች በፍጥነት እንዲተገበሩ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸው፤ የሀገራቱ ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምክር ቤቶቹም በጋራ ለመሥራት ዝግጁ ናቸው ብለዋል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት፣ ስራ ስምሪትና የቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ እና ቻይና በተለያዩ ዘርፎች ስትራቴጂካዊ ትብብር እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

በሁለቱ ሀገራት መካከል ላለው በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ትልቅ ዋጋ እንደሚሰጡ በማንሳት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ዓመታት በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ሪፎርም ማድረጓን ለቻይና ልዑክ አብራርተዋል፡፡
በሪፎርሙ የመንግስትን አገልግሎት በዲጂታል የታገዘ በማድረግ አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን መልካም አስተዳደርን የማስፈን ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የፖለቲካ ሪፎርሙ ሰላማዊ ትብብርና ተሳትፎን የሚያረጋግጥ ምህዳር በመፍጠር የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አሳድጓል ብለዋል፡፡