AMN – ሰኔ 19/2018 ዓ.ም
ከሰባት ዓመታት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለአፍሪካ ብሎም ለተቀረው ዓለም ትልቅ ተምሳሌት ሆኗል።
በመርሃ ግብሩ እስካሁን ድረስ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፣ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄም 8 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሃ ግብር በይፋ እየተካሄደ ይገኛል።
ይህ መርሃ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ የተያዘውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የመከላከል ራዕይ እያሳካ ከመሆኑም በላይ፣ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት ለተቀመጠው ዕቅድ ጠንካራ መሠረት በመጣል ላይ ነው።
በኢትዮጵያውያን ትብብር የተገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካ ግዙፉ የታዳሽ ኃይል መሠረተ ልማት ሲሆን፣ ከሀገሪቱ አልፎ ቀጣናውን በኃይል እያስተሳሰረ ይገኛል።
ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ የውሃ፣ የንፋስ፣ የፀሐይ እና የጂኦተርማል የታዳሽ ኃይል መሠረተ ልማት ስኬት ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን በማሳለጥ ረገድ ከፍተኛ ውጤት እያስገኘ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በተካሄደው ”ኢትዮጵያ ታከናውናለች” ጉባኤ ላይ የተገኙት፣ በመንግሥታቱ ድርጅት በምክትል ዋና ጸሐፊ ማዕረግ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ክላቨር ጋቴቴ፤ አፍሪካ በዓለም አቀፍ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ምክንያት ከፍተኛ ተጽዕኖ እያስተናገደች ትገኛለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ግን እነዚህ ዓለም አቀፍ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ያልበገሯትና ፈጣን ዕድገት የምታስመዘግብ አፍሪካዊት ሀገር ለመሆን መብቃቷን ገልጸዋል።
ይህ የኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያና የቁርጠኛ አመራር ውጤት መሆኑን በመግለጽ፣ የሀገሪቱ የአረንጓዴ አሻራ እና ዘላቂ የልማት መርሃ ግብሮች ተምሳሌታዊ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ዋና ጸሐፊው አክለውም፣ አፍሪካ ለዓለም አቀፍ ችግሮችና ለአየር ንብረት ለውጥ የመፍትሔ አካል መሆን እንደምትችል ኢትዮጵያ በተግባር እያሳየች መሆኗን ገልጸው፤ ሀገሪቱ በንጹሕ የትራንስፖርት አማራጭም ጭምር የአፍሪካ ተምሳሌት መሆን ችላለች ብለዋል።

እ.ኤ.አ በ2027 በኢትዮጵያ አዘጋጅነት በአዲስ አበባ የሚካሄደው የኮፕ 32 ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባዔ፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ከመከላከል ባሻገር በአፍሪካ ግዙፉን የታዳሽ ኃይል መሠረተ ልማት በመገንባትና ቀጣናውን በኃይል በማስተሳሰር እያበረከተች ያለው ጉልህ አስተዋጽኦ በጎላ ሁኔታ የሚወጣበት መድረክ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ባስተላለፉት መልእክት፤ በዚህ ዓመት 8 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ግብ አስቀምጠን፣ ከፍ ወደተደረገው 65 ቢሊዮን ችግኞች የመድረስ ትልማችንን ለማሳካት በጽናት እየገሰገስን እንገኛለን ማለታቸው ይታወሳል።
በመጨረሻም መላው ኢትዮጵያውያን ንቅናቄውን ተቀላቅለው ለመጪው ትውልድ አረንጓዴ ዐሻራቸውን እንዲያኖሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በወንድማገኝ አሰፋ