AMN-ሰኔ 18/2018 ዓ.ም
ብራዚል በማያሚ ስታዲየም ስኮትላንድን 3ለ0 ስትረታ ያዩ ደጋፊዎች ደስታቸው የተለየ ነበር።
ደስታቸውን የበለጠ ከፍ ያደረገላቸው 76ኛው ደቂቃ ላይ ኔይማር ተቀይሮ ሲገባ በማየታቸውም ጭምር ነው።
ኔይማር ጁኑዮር ተቀይሮ እንደሚገባ የስታዲየሙ አስተዋዋቂ ስሙን ሲጠራ በርካታ ደጋፊዎች ከወንበራቸው ተነስተው በክብር ተቀብለውታል።
ደጋፊዎቹ ሦስት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ የብሔራዊ ቡድኑን መለያ አጥልቆ ለማያውቀው ኮከባቸው ያላቸውን ክብር አሳይተዋል።
በእርግጥ ኔይማር በሁሉም ደጋፊዎች ያለ ልዩነት የሚሞገስ ተጫዋች አይደለም። ከእርሱ የጠበቅነውን ያህል አላገኘንም በሚል የሚነቅፉት ቁጥራቸው ጥቂት አይደለም።

ፔሌ ፣ ዚኮ ፣ ጋሪንቻ ፣ ሮማሪዮ ፣ ቤቤቶ ፣ ሪቫልዶ ፣ ሮናልዶ ሊውስ ናዛሪዮ ፣ ሮናልዲኖ ሌሎችም ሀገራቸውን ያደረሱበት ከፍታ ላይ እንዲያደርስ ምናልባት ከአቅሙ በላይ የሆነ ኃላፊነት ያሸከሙት ደጋፊዎች አልጠፉም።
የአምስት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ብራዚል በኔይማር ዘመን የነበራት ትውልድ ግን ጥራቱ ከፍ ያለ እና ስኬቷን ማስቀጠል የሚችል አልሆነም። ኔይማር ካለው ተሰጥኦ መነሻ የቡድኑ ሸክም ወደ እርሱ ቢተላለፍም ከብዶት የተደናቀፈባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው።
በተለይ ባርሰሎናን ለቆ ፓሪሰን ዠርማ ከተቀላቀለ በኋላ የብቃቱ ከፍታ ላይ ለመድረስ ተቸግሯል። በተደጋጋሚ የገጠመው ጉዳትም ዓለም ተሰጥኦን ጠግቦ እንዳይመለከት መሰናክል ሆኗል።
አሁን 34 ዓመቱ ላይ የሚገኘው ኔይማር በብሔራዊ ቡድን ያሳካው ትልቁ ውጤቱ በ2016 ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ያስገኘበት እንዲሁም ፊፋ አሁን ላይ የሰረዘው ኮንፌዴሬሽን ካፕን በ2013 ያገኘበት ብቻ ነው።
ኔይማር ጁኑዮር የብሔራዊ ቡድን ስኬቱ በዚህ ብቻ እንዳይገደብ ያለውን ሁሉ ሰጥቷል። ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ታሪካዊ ተጫዋቾችን በልጦ በ79 ግቦች የሀገሪቱ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኗል። እነዚህ ግን የዓለም ዋንጫ አላመጡለትም።

አሁን በካርሎ አንቸሎቲ የመጨረሻ ዕድል ተሰጥቶታል። በጉዳት የመጀመሪያ ሁለቱ ጨዋታዎች አልፈውት ተመልሷል። እንደከዚህ ቀደሙ ዋናው ሰው ሆኖ ጨዋታ ባይጀምርም ለቡድን አንድነት እንዲሁም ልምዱን ለማካፈል ይጠቅማል ተብሎ ታምኖበታል።
ስኮትላንድን በገጠሙበት ጨዋታ በማቴኡስ ኩኝሃ ተቀይሮ ሲገባ ደጋፊዎች ያሳዩት ፍቅር ለእርሱ ትልቅ ተነሳሽነት ይሰጠዋል። ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ቤተሰቦቹ ሲያቀና ስሜቱን በእንባ ገልጿል።
በጉልበት ጉዳት ምክንያት ለ981 ቀናት የሚወደውን መለያ አለማጥለቅ ለእርሱ ከባድ ነበር።
“ኔይማር ያለው ተሰጥኦ ቡድኑን ያግዛል ፤ ተቀይሮ ከገባ በኋላ ጥሩ ተጫውቷል ፤ እርሱ የሀገሩን መለያ ለማጥለቅ የተለየ ተነሳሽነት አይፈልግም ፤ ሁሌም ሀገሩን ለመርዳት ዝግጁ ነው ፤ 34 ዓመቱ ላይ ቢገኝም በልጅነቱ የነበረው ተነሳሽነት አሁንም አብሮት አለ” ሲሉ ካርሎ አንቸሎቲ ከጨዋታው በኋላ በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
ኔይማር ለዓመታት የተመኘውን የዓለም ዋንጫ ዘንድሮ ያሳካ ይሆን? ሀሳባችሁን አጋሩን ።
በሸዋንግዛው ግርማ