AMN- ሰኔ 18/2018 ዓ.ም
በክረምት ወራት ቤትን ለማሞቅ በቤት ውስጥ ከሰል ማቀጣጠል በብዙዎቻችን ዘንድ የተለመደ ነው።
ይሁን እንጂ ይህ ተግባር በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለከባድ የጤና ችግር አልፎም ለህልፈት እየዳረገ ይገኛል።
ከሰል በሚቀጣጠልበት ወቅት “ካርቦን ሞኖክሳይድ” የተባለ መርዛማ ጋዝ ይፈጠራል፤ በዚህ ወቅት ጥንቃቄ ካልተደረገ ለጤናችን አስጊ የሆኑ በርካታ ችግሮች ያጋጥማሉ፡፡
በካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የድንገተኛ እና ጽኑ ሕሙማን ስፔሻሊስት ሐኪም ዶክተር ሞላልኝ ውብአንተ፣ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ጉዳዩን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ከሰል በሚቀጣጠልበት ጊዜ ካርቦን ሞኖክሳይድ የተባለ አደገኛ ጋዝ ይለቀቃል።
ይህ ጋዝ ቀለም የለውም፣ በአይን አይታይም፤ ይህ አደገኛ ጋዝ ወደ ሰውነታችን ሲገባ፣ በደም ውስጥ ያለው ኦክሲጅን የመሸከም አቅምን በማዳከም የሰውነት ሕዋሳት፣ በተለይም ልብ እና አንጎል በአግባቡ እንዳይሰሩ ያደርጋል።
በከሰል ጭስ የታፈነ ሰው የሚያሳያቸው ምልክቶች

ዶክተር ሞላልኝ እንደገለጹት፣ በከሰል ጭስ መመረዝ ምልክቶች በተለይ ቤት በተዘጋ ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት ይከሰታሉ።
የከሰል ጭስ ወደ ሰውነታችን ሲገባ ከሚያሳያቸው ምልክቶች መካከል- ኃይለኛ ራስ ምታት፣ ማቅለሽለሽ እና ማስመለስ፣ ትንፋሽ ማጠር፣ የእንቅልፍ ስሜት እና ድካም፣ ራስን መሳት ይጠቀሳሉ፡፡
ምንም እንኳን የከሰል ጭስ ለሁሉም ሰው አደገኛ ቢሆንም፣ ሕፃናትን፣ አረጋውያንን፣ ሥር የሰደደ ሕመም ያለባቸውን ሰዎች እና ነፍሰጡር እናቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለከፋ ጉዳት ያጋልጣቸዋል፡፡
መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎች፡-

አደጋውን ለመቀነስ ከሰል በሚጠቀሙበት ጊዜ በሮች እና መስኮቶች ክፍት መሆናቸውን ማረጋገጥ እና አየር እንዲዘዋወር ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ያሳስባሉ፡፡
ከመተኛት በፊት የከሰል እሳቱን ሙሉ በሙሉ አጥፍቶ ከቤት ውጭ ማስወጣት የግድ መሆኑንም ዶክተር ሞላልኝ ተናግረዋል፡፡
አንድ ሰው የከሰል መመረዝ ምልክቶች ካጋጠመው ወዲያውኑ ከክፍሉ ወጥቶ ንጹህ አየር መውሰድ፣ ህመሙ ከበረታበትም በፍጥነት አቅራቢያ ወደ ሚገኝ የጤና ተቋም መሄድ ያስፈልጋል ሲሉም መክረዋል፡፡
የክረምት ቅዝቃዜን ለመከላከል የምናደርገው ጥረት የሕይወት ዋጋ እንዳያስከፍለን፣ ከሰል ስንጠቀም በጣም መጠንቀቅ የሕይወት መዳኛ ቁልፍ መሆኑንም ዶክተር ሞላልኝ በአጽንኦት አስገንዝበዋል፡፡
በፍሬሕይወት ብርሃኑ