የአህጉሪቱ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን ልብ የማረከችው አዲስ አበባ

You are currently viewing የአህጉሪቱ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን ልብ የማረከችው አዲስ አበባ

AMN- ግንቦት 3/2018 ዓ.ም

ለረጅም ዓመታት በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ስለ ኢትዮጵያ የሚሰጠው ምስል በአንድ ወገን ብቻ የተወሰነ ሆኖ ዘልቋል። ዛሬ ግን በአዲስ አበባ የአፍሪካ የታሪክ ነጋሪዎች፣ የዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎች እና የባህል አምባሳደሮች ይህንን ታሪክ እየቀየሩት ይገኛሉ።

አለም ዓቀፍ ሁነቶችን ከሽና እያቀረበች የምትገኘው የአፍሪካውያን የልብ ትርታ አዲስ አበባ የመጀመሪያው የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ (ASMIS-2026) በድምቀት አከናውናለች።

ከአዲስ አበባ የከተማ እንቅስቃሴና የልማት ትሩፋቶች ጅምሮ እስከ ተወዳጁ የኢትዮጵያ ቡና ስነ-ስርዓት ድረስ አህጉሪቱን ጠንቅቀው በሚያውቁ ሰዎች እይታ ከተማዋ በአዲስ መልክ ተቃኝታለች።

አዲስ አበባ በገባሁበት ቅጽበት ያጋጠመኝ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ እጅግ አስደናቂ ነበር ስትል ከናሚቢያ የመጣችው ዝነኛዋ ማሪያ ኖ አዲስ አበባ እንደገባች የገጠማትን አስገራሚ ሁኔታ ገልፃለች።

አክላም ከተማዋ ንጹህ፣የተቀናጀ መሰረተ ልማቷም በሚገባ ከነዋሪው ፍላጎት ጋር ተቀናጅቶ የተሰራ መሆኑን ገልጻ፣ይህም ለተቀረው አፍሪካ ትልቅ ምሳሌ የሚሆን መሆንን መስክራለች።

ኢትዮጵያ ለዘመናዊ የአፍሪካ ከተሞች ግንባታ እንደ አርአያ የምትታይ መሆኑንም አፅንኦት ሰጥታለች። ከመሰረተ ልማቱ ባሻገር ፣የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ልዩ የሚያደርገው ጥልቅ የሆነው ባህላዊ እሴት መሆኑን ገልፀዋል።

ለብዙዎቹ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የኢትዮጵያ ቡና ስነ-ስርዓት ትልቅ የክብር መግለጫም ሆኗል። ሌላኛው የይዘት ፈጣሪ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እንደደረሰ መጀመሪያ የፈለገው ያንን ተፈጥሯዊ ቡና እንደነበረ ገልጾ፣ኢትዮጵያ እድገትን እና ጥንታዊ ማንነትን በሚገርም ሁኔታ አስተሳስራ የያዘች ሀገር መሆኗን ተናግሯል።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ያላት የፖለቲካ እና የማህበራዊ ፋና ወጊነት ሚና ላቅ ያለ መሆኑንም የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎቹ ያገኙት ትልቁ ትምህርት መሆኑንም አብራርተው፣ በቅኝ ግዛት አለመያዟ በአፍሪካውያን ዘንድ ልዩ ስፍራ እንዲኖራት ማድረጉንም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ዜጋ ተኮር የልማት ስራ ምን እንደሆነ እና ሀገርንና ከተማን እንዴት መጠበቅ እንደሚቻል ለሌሎች የምታሳይ የአፍሪካ እናት ሀገር መሆኗን በተግባር ገልጣለች ሲል ሌላኛው ተሳታፊም ይናገራል።

አዲስ አበባ ለሁሉም የአፍሪካ ሀገራት እንደ ማሳያ ለመሆን ብቁ ከተማ መሆኗንም አፅንዖት ሰጥቶበታል።

ከጉባኤው መጠናቀቅም በኋላ እነዚህ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ተከታዮቻቸው የጉዞ ታሪካቸውን እያጋሩ ሲሆን ኢትዮጵያም ቀዳሚ የቅርስና ቱሪዝም መዳረሻ ለመሆን ውጤታማ ስራ እሰራችና እየተጋች መሆኑንም እያጋሩ ይገኛል።

መልዕክቱ ግልጽ ነው ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ብቻ ሳይሆን ኩሩ አፍሪካዊ መሆንን ለመማር የምትመረጥ ከተማ አዲስ አበባ ናት የሚል ነው ።

በሚካኤል ህሩይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review