AMN- ግንቦት 4/2018 ዓ.ም
ከስደት ተመላሿ መቅደስ መንበረ ተስፋ መቁረጥ ደጃፏ ድረስ መጥቶ የነበረ ቢሆንም ፣ ልጇን በካርቶን ላይ አስተኝታ ቡና እያዞረች የምትሸጥ እናት ነበረች፡፡ ዛሬ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ተጠቃሚ በመሆኗ ብዙ ጫና ተቃሎላታል።
በከተማዋ የተጀመሩት የህጻናት ማቆያ ማዕከላት የአንድን ህጻን አካላዊና አእምሯዊ እድገት ከመቀየር ባለፈ፣ የሴቶችን የኢኮኖሚ ነጻነት ለማረጋገጥ በመንገድ ከፍተዋል።
የመቅደስ ልብ የሚነካ ታሪክ ከስደት ስትመለስ ይጀምራል በወቅቱ እጇ ላይ ምንም አልነበረም።ነገር ግን ተስፋ ባለመቁረጥ ያገኘችውን ስራ ሁሉ ትሰራ ነበር።
“ራሴን አስተካክዬ አንዳንድ ስራዎችን ጀመርኩ፤ በየሰው ቤቱም እየተንቀሳቀስኩ እሰራ ነበር። በኋላ ግን ቡና ማዞር ጀመርኩ” ስትል የትግሏን መጀመሪያ ታስታውሳለች።
ነገር ግን ትልቁ ፈተና የነበረው የስራው ሁኔታ ሳይሆን፣ ገና የዘጠኝ ወር ጨቅላ የነበረችውን ልጇን የምታሳርፍበት ቦታ ማጣቷ ነበር። “ልጄን ካርቶን ላይ አንጥፌ አስተኝቻት፣ እሷ እዛው እየተጫወተች እኔ ቡና አዞራለሁ” ስትል ታስታውሳለች።

በአንድ ወቅት ልጇ በካርቶን ላይ ተኝታ የሚያልፉ ሰዎች ይመለከቷታል። በሁለተኛው ቀንም በዛው ሁኔታ ሲያገኟቸው “እንዲህ ያለ የህጻናት ማቆያ መኖሩን አልሰማሽም?” የሚል ጥያቄ ሰነዘሩላት። እናት መረጃው ቢኖራትም እንዴት እንደምትጠቀምበት ግን አታውቅም ነበር።
በተሰጣት መመሪያ መሰረት የልደት ሰርተፍኬት፣ መታወቂያ እና የክትባት ካርድ በመያዝ ወደ ወረዳዋ ሴቶችና ህጻናት ጽህፈት ቤት አመራች። በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥም ባለሙያዎች ቤቷ ድረስ መጥተው ሁኔታዋን ካጠኑ በኋላ ልጇን ወደ ማቆያው አስገቡላት።
ልጅቷ ወደ ማዕከሉ ከመግባቷ በፊት የነበረው ሁኔታ አስቸጋሪ ነበር። “ዘጠኝ ወር ሙሉ ዳዴም አትልም፣ ቆማም አትሄድም ነበር። ሁልጊዜ የታዘለች ስለሆነች የመንቀሳቀስ እድል አልነበራትም” ትላለች እናት መቅደስ።
ወደ ማዕከሉ ከገባች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ዳዴ ማለት ጀመረች፣ በአስራ አንድ ወሯ ወንበር እየያዘች መራመድ እና በአንድ ዓመት እንደማንኛውም ህጻን በራሷ መሄድ ጀመረች።
ዛሬ ያቺ በካርቶን ላይ ትተኛ የነበረች ህጻን በጣም ንቁ እና ፈጣን ሆናለች። ከሞግዚቶቿ ጋር የዋለችውን ውሎ፣ የዘመሩትን መዝሙር እና የበሉትን ምግብ ሁሉ ለእናቷ ትተርካለች።

ሕጻናት ማቆያ መግባቷ ለህጻኗ ብቻ ሳይሆን ለእናቷም ትልቅ እፎይታን ሰጥቷታል። “ልጄን አዝዬ ስሰራ ወገቤን ያመኝ ነበር፣ የራስ ምታትም ነበረብኝ ለመስራት ፍላጎት ባይኖረኝም ለኑሮ ስል ግን እገፋው ነበር” የምትለው መቅደስ ፣ አሁን ግን ያ ችግር እንደተቀረፈላት ትናገራለች።
“አሁን በነጻነት፣ ሳይደክመኝ እንደፈለኩኝ ተሯሩጬ እሰራለሁ ፣ ትልቅ መንፈሳዊ እርካታ ነው ያገኘሁት” ስትል ያገኘቸውን ጥቅም ትገልጻለች።
ይህ እድል እናቶች ራሳቸውን እንዲለውጡ የተሰጠ መሆኑንም ነው መቅደስ የምትናገረው።

የአዲስ አበባ አስተዳደር ከምችለው በላይ፣ ከአቅሜ በላይ የሆነ ችግር ነው የተፈታልኝ ስትል ይህንን ትልቅ የቤት ስራ ላቃለሉላት ከንቲባ አዳነች አቤቤ እድሜና ጤና ይስጥልን ስትል መልካም ምኞቷን ትገልጻለች። ብዙ የእኔ ዓይነት ችግር ላለባቸው ሴቶች ደርሰዋል ብላለች።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ