AMN ግንቦት 4/2018
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ብሔራዊ መግባባት የሰፈነባትን ሀገር ለትውልድ ለማስረከብ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የፖለቲካ ቅራኔዎችን በሃሳብ የበላይነት የተመሰረተ ውይይት በማድረግ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው አጀንዳ ነው።
ለዚህም የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች፣ የፌደራል ተቋማትና በውጭ ከሚኖሩ ዜጎች የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታን በስኬት አጠናቋል።
በአሁኑ ወቅትም ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ማካሄድ የሚያስችሉ የመጨረሻ የዝግጅት ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
ዜጎችም ይህን ታሪካዊ ዕድል በስኬት በመቋጨት በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ጠንካራ ሀገረ መንግስትና ሰላማዊ የፖለቲካ ባህል የመገንባት ኃላፊነት አለባቸው።
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር የሚያስችል ወሳኝ ዕድል ነው።

በዚህም በሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ ወቅት የነቃ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይም በዋናው ሀገራዊ ጉባኤ ላይ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ሰናይት ቀበታ እንደገለጹት፤ ቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገር እንዲረከብ ዘላቂ ሰላምና አንድነትን የሚያፀና ምክክር ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
አቶ ገቢሳ በየነ በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ምክክር ለዘመናት ሲንከባለሉ ለመጡ ጉዳዮች ዘላቂ እልባት መስጠት የሚያስችል ታሪካዊ ዕድል መሆኑን ገልጸዋል።

በዋናው ሀገራዊ የምክክር ሂደትም ለሀገር የሚበጁ ሃሳቦችን በማዋጣት ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት ይጠበቅብናል ብለዋል።
ሌላኛዋ የመዲናዋ ነዋሪ ታደለች ደግፌ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን የሚያመጣ ወሳኝ አጀንዳ በመሆኑ ለስኬቱ በትብብር መስራት ይኖርብናል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የተናገሩት ደግሞ ወንድማገኝ በቀለ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው።

ሀገራዊ የምክክር ሂደቱን በስኬት በመቋጨት ቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን እንዲረከብ ማድረግ አንደሚያስፍልግም ገልጸዋል።
እንዳሻው ነጋሽ የተባሉ አስተያየት ሰጪም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ መግባባትን ለማምጣት ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል።