AMN- ግንቦት 5/2018 ዓ.ም
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት ዛሬ የዓለም አትሌቲክስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሚስተር ጆን ረጂዮን ጋር በስፖርት ስትራቴጂካዊ ዕድሎች ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት አድርገናል ብለዋል፡፡

የውይይታችን ዋና ዓላማም በሀገራችን ኢትዮጵያ የ2028 አልቲሜት ሻምፒዮንሺፕ እና የ2031 የአትሌቲክስ የዓለም ሻምፒዮና ለማዘጋጀት የቀረበውን ጥያቄ መነሻ በማድረግ በአዲስ አበባ እየተገነቡ ያሉ እስቴዲየሞች እና ሌሎች የስፓርት መሰረተ ልማቶችን መገምገምን መሰረት ያደረገ ነው።
በቅርቡ ከተማችን ከሶስት በላይ ዓለም አቀፍ የስፖርት ሁነቶችን በብቃት ማስተናገዷን እና ታላላቅ የስፖርት ሁነቶችን ለማስተናገድ ብሎም ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በሚያስችል የስፖርት መሰረተ ልማት ግንባታ፣ ስልጠናዎችን በማስፋፋት እና የህዝባችን እንግዳ ተቀባይነትን ለልዑካኑ ገለጻ አድርገናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የዓለም አትሌትክስ ዋና ስራ አስፈፃሚው በበኩላቸው፤ በአዲስአባባ እየታየ ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ እና መንግስት የስፓርት ሁነቶችን ለማካሄድ ላሳየው ቁርጠኝነት ያላቸውን አድናቆት በመግለፅ በአጋርነት ለመስራት ያላቸውን ፍላጐት አሳውቀውናል፤ ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ ወደ ከፍታ ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡