AMN-ሚያዝ 15/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ታምርት የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ” ለሁለተናዊ ሉዐላዊነት ኢትዮጵያ ታምርት ” በሚል መሪ መልዕክት ሚያዚያ 18/ 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 4ኛ አመትን አስመልክቶ ከተዘጋጁ መርሃ ግብሮች መካከል የ10 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ አንዱ መሆኑን የጠቆሙት የኢትዮጵያ ታምርት 2018 የሩጫ ውድድር ሰብሳቢ አቶ አብዱልፈታ ዩሱፍ፣ ዓላማውም አምራች ኢንዱስትሪዎች በስፖርቱ ዘርፍ መዋዕለ ንዋያቸውን አፍስሰው አስፈላጊውን ምርቶች በማምረት ድጋፍ እንዲያደጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሀገር ውስጥ አምራቾች የተመረቱ የስፖርት ዕቃዎችን ለማስተዋወቅ እንዲሁም አስፈላጊውን የገበያ ትስስር ለመፍጠር ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑንም አክለዋል ገልጸዋል፡፡

የ10 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫው መነሻና መዳረሻውን መስቀል አደባባይ የሚያደርግ መሆኑን ያሳወቁት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተሳትፎ እና ውድድር ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ጊዜ አድነው፣ ከ500 በላይ የሚሆኑ ታዋቂ አትሌቶች በሚሳተፉበት የሩጫ ውድድር በሁለቱም ጾታዎች ተወዳድረው ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ለሚወጡ ተወዳዳሪዎች በኢትዮጵያ ከፍተኛ የተባለውን የ550 ሺ፣ የ300 ሺ እና የ200 ሺ የብር ሽልማት መዘጋጀቱ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ታምርት የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫን በዓለም አትሌቲክስ ህግ መሰረት እንዲመራ በማድረግ ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን እንዲያገኝ እየተሰራ መሆኑን አቶ ጊዜ አድነው ገልፀዋል።
በዚህ ውድድር 10 የሚሆኑ ክለቦች ተመዝግበው ለውድድሩ መዘጋጀታቸው የተገለፀ ሲሆን በኢትዮጵያ ታምርት የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ከ15ሺ በላይ ተወዳዳሪዎች እንደሚሳተፉበትም ይጠበቃል።
በአሸናፊ በላይ