AMN- ግንቦት 6/2018 ዓ.ም
ማህበራዊ ፍትህን የምናነግስበት አንዱ የተስፋ ብርሃን የምገባ ፕሮግራማችን፣ ዛሬ በልደታ ክፍለ-ከተማ ለክፍለ-ከተማው 3ኛ የሆነ 29ኛውን የተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከል ገንብተን ስራ አስጀምረናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበጎነት መንደር፤ ተጨማሪ የበጎነት ተግባር! መከናወኑን ገልጸዋል፡፡
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ በገነባነው 492 ቤቶች ውስጥ ለሚኖሩ 2 ሺህ 460 ለሚሆኑ ነዋሪዎቻችን እፎይታ በሆነው በተለይም በርካታ አረጋውያን፣ ለማህበራዊ ችግር የተጋለጡና ድጋፍ ለሚሹ ወገኖቻችን እንዲሁም ለልማት ተነሺዎች በሚኖሩበት የበጎነት መንደር ውስጥ ድጋፍ ለሚገባቸው ወገኖች ዛሬ ምገባ ያስጀመርንበት የምገባ ማዕከል ተጨማሪ የበጎነት ስራ ነው ብለዋል።

ንፁህ፣ ትኩስ ምግብ በቀን አንድ ጊዜ የሚቀርብባቸው በሁሉም ክፍለ ከተማ 29 የምገባ ማዕከላት ውስጥ መመገብ ስለሚቻል፤ ለችግር የተጋለጡ ወገኖቻችን ምግብ ፍለጋ ወደ ጎዳና የሚያስወጣ ምክንያት በከተማችን ስለሌለ፤ በማዕከላቱ በመገኘት መመገብ ትችላላችሁ ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በዚህ የበጎነት መንደር የስራ እድል የተፈጠረባቸው የእንጀራ መጋገሪያ ማዕከል፣ የልብስ ስፌት፣ የፀጉር ስራና የልጆች መጫወቻ ለነዋሪዎቹ ሌላኛው የእፎይታ ምንጭ ናቸው በማለትም ገልጸዋል።
ሁሌም ማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ ያለው ዳሽን ባንክ፣ ጥሪአችንን ተቀብሎ ለማዕከሉ ግንባታ እና በቀጣይም ለመመገብ ላደርገልን ድጋፍ በራሴና በተጠቃሚዎች ስም ክልብ እመሰግናለሁ ብለዋል።