በጎዴ እየተገነባ ያለው የ3 ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ በአጠረ ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

You are currently viewing በጎዴ እየተገነባ ያለው የ3 ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ በአጠረ ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

AMN – ግንቦት 09/2018 ዓ.ም

በሶማሌ ክልል ጎዴ አካባቢ እየተገነባ የሚገኘው የ3 ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝና በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሮጀክቱን የስራ ሂደት ዛሬ በአካል ተገኝተው ከጎበኙ በኋላ በሰጡት መግለጫ ፣ ፋብሪካው ግንባታው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በ40 ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ለህዝብ ቃል ተገብቶ የነበረ ቢሆንም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ፍላጎት እጅግ እየጨመረ በመምጣቱ ፕሮጀክቱን ይበልጥ ለማፋጠን መታቀዱን ገልጸዋል።

አሁን ባለው ሂደት ግንባታውን ከ40 ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ አጠናቀን ለሀገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብና ከሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚተርፈውን ደግሞ ለውጭ ገበያ ለመላክ ግንባታውን ከሚያከናውኑት ባለሀብት አሊኮ ዳንጎቴ ጋር ጥሩ ስምምነት ላይ ደርሰናል ሲሉ ነው የገለጹት።

ቀደም ሲል በሃሳብ ደረጃ የነበረው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት አሁን ላይ በተግባር ተጀምሮ በጥሩ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በቀጣዮቹ 3 እና 4 ወራት ውስጥ ትልቅ ለውጥ እንደሚመዘገብ ጠቁመዋል።

ለአምስት ሺህ ሰራተኞች አገልግሎት የሚሰጥ የመኖሪያ መንደር ግንባታ እየተካሄደ ሲሆን፣ የመኖሪያ ቤቶቹ ግንባታ እስከ መጪው መስከረም ወር ድረስ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ተናግረዋል።

የውሃ ማስተላለፊያ መስመሮችን የመዘርጋት፣ ከፍተኛ ቦታዎችን ዝቅ የማድረግና ዝቅተኛ ቦታዎችን በመሙላት መሬቱን ለፕላንቱ ዝግጁ የማድረግ ስራዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተከናወኑ እንደሚገኙም አብራርተዋል።

ለፋብሪካው ግንባታ የሚያስፈልጉ በርካታ ማሽነሪዎችና ቁሳቁሶች ተገዝተው ወደ ስፍራው እየገቡ መሆናቸውንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ያስረዱት።

ባለሀብቱ አሊኮ ዳንጎቴ የገቡትን ቃል ጠብቀው ገንዘባቸውን ፣ ጊዜያቸውንና ባለሙያዎችን በከፍተኛ ሁኔታ እያፈሰሱ እንደሚገኝ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግስትም በበኩሉ የፌደራልና የክልል የስራ ኃላፊዎችን በማስተባበር የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ታደሠ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review