AMN – ግንቦት 09/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወነው አስደናቂ የኮሪደር ልማት ሥራ፣ ከተሞችን እንዴት ለዜጎች ምቹ፣ ውብና ተስማሚ አድርጎ መገንባት እንደሚቻል ለመላው ዓለም ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን እንግሊዛዊው ጋዜጠኛ ዳንኤል ካርል ገለጸ።
መቀመጫቸውን በእንግሊዝ ሀገር ያደረጉ ስምንት ዓለም አቀፍ ምሁራንና ጋዜጠኞች በአዲስ አበባ ፈጣን የለውጥ ጉዞ ላይ ጥናት ማካሄዳቸውን ጋዜጠኛው የገለጸ ሲሆን፣ ይህ ጥናታዊ ግኝታቸውም በቅርቡ መጽሐፍ ሆኖ ታትሟል።

በጥናቱ ላይ በንቃት የተሳተፈው ጋዜጠኛ ዳንኤል ካርል፤ ከዓመታት በፊት የምናውቃት አዲስ አበባ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ባከናወነችው ዘመናዊ የከተማ ልማት ግንባታ በአሁኑ ወቅት ዓለም ሁሉ ሊያያቸውና ሊጎበኛቸው ከሚጓጓላቸው ከተሞች ተርታ መሰለፏን ገልጿል።
ከተማዋ በአሁኑ ወቅት በአረንጓዴ ሽፋኗ፣ በበለጸገ ውበቷ እንዲሁም በእግርና በሳይክል ለመጓዝ ባላት ምቹነት እንደ ባርሴሎና፣ ሞናኮና ዱባይ ካሉ የዓለም ታዋቂ ከተሞች ጋር እንደምትመሳሰል ጋዜጠኛው ጠቁሟል።
መዲናዋን በዚህ ፍጥነት ለመለወጥና ለቀጣይ ትውልድ የሚተርፍ ታላቅ አሻራ ለማስቀመጥ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር እንዲሁም የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ራዕይ፣ የፖለቲካ ቁርጠኝነትና የላቀ አመራር ቀዳሚውን ሚና መጫወቱን ጋዜጠኛው ገልጿል፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃሉ ተብለው የማይታሰቡ ግዙፍና ውስብስብ ፕሮጀክቶች፣ በተሟላ ቁርጠኝነትና ጥራት ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸው ለመሪዎቹ ስኬት ህያው ማሳያ መሆኑም ተገልጿል።
ይህ በአዲስ አበባ የተከናወነው የከተማ ልማት ሥራ በተለይም የአፍሪካ መሪዎች ከተሞቻቸውን ለዜጎቻቸው በሚመጥን መልኩ እንዴት ማልማት እንዳለባቸው የሚያሳይ ተመራጭ ተግባራዊ ሞዴል መሆኑ ተብራርቷል።

በታተመው መጽሐፍ ላይ በሰፊው እንደተመለከተው፤ አዲስ አበባ በኮሪደር ልማትና በከተማ ግንባታ ሥራዎቿ ውስጥ ዘመናዊ የጤና እና የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን በምርጥ ሁኔታ አጣጥማ መገንባት ችላለች።
ከዚህም ባለፈ በአሜሪካና በምዕራብ አውሮፓ ታዋቂ ከተሞች የሚታየውን ዓይነት ለአይን ማራኪ የሆነ የአረንጓዴ ሽፋንና የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎችን መፍጠር መቻሏ፣ ከአፍሪካ አልፎ መላው ዓለም ከአዲስ አበባ የለውጥ ጉዞ ሊማር እንደሚገባ በምሁራኑ ጥናት ተመላክቷል።
በበረከት ጌታቸው