AMN-ሰኔ 27/2018 ዓ.ም

በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 48 ሀገራትን ያሳተፈው የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ 32 ሀገራትን ሸኝቶ 16 ብቻ አስቀርቷል። በውድድሩ የቀሩ ሃገራት ወደ ሩብ ፍፃሜ ማስገባት የሚያስችላቸውን የጥሎማለፍ ዙር ዛሬ ይጀምራሉ። ካናዳ ከ ሞሮኮ ፤ ፓራጓይ ከ ፈረንሳይ የስፖርቱ አፍረቃሪ ለማየት የጓጓላቸው የዕለቱ ጨዋታዎች ናቸው።
ካናዳ ከ ሞሮኮ

ሦስተኛ የዓለም ዋንጫዋን እየተሳተፈች የምትገኘው የጣምራ አዘጋጇ ካናዳ ታሪካዊ ውድድር እያሳለፈች ትገኛለች። በአሜሪካዊው አሰልጣኝ ጄሴ ማርሸ የምትመራው ሀገር ለጥሎ ማለፍ ስትበቃ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
በ32ቱ የማጣሪያ ዙር ደቡብ አፍሪካን 1ለ0 በማሸነፍ ጉዞዋን ያስቀጠለችው ካናዳ ዛሬ ደግሞ ሌላኛዋን የአፍሪካ ሀገር ሞሮኮ ትገጥማለች።
ለአፍሪካ ትልቅ ተስፋ የሆነችው ሞሮኮ ኔዘርላንድስን በመለያ ምት አሸንፋ ነው ለዛሬው ጨዋታ የበቃችው። ምንም እንኳን ጨዋታው ወደ መለያ ምት ቢያመራም ሞሮኮ ኔዘርላንድስ ላይ የወሰደችው ብልጫ አስገራሚ ነበር።

ለአፍሪካ ሀገራት የማሸነፍ ቅድመ ግምት ሲሰጥ መመልከት የተለመደ አይደለም። ሞሮኮ ግን በምድብ ጨዋታዋ ከብራዚል ጋር አቻ ስትለያይ ኔዘርላንድስንም ስታሸንፍ የተመለከቱ የስፖርቱ ባለሞያዎች የዛሬውን ጨዋታ የማሸነፍ ዕድል ለሞሮኮ ሰጥተዋል።
ሞሮኮ እና ካናዳ በታሪካቸው አራት ጊዜ ተገናኝተው የሰሜን አፍሪካዋ ሀገር ሽንፈት አልገጠማትም። ሦስቱን አሸንፋ በአንዱ አቻ ተለያይታለች።
ሁለቱ ሀገራት ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት ሞሮኮ ግማሽ ፍፃሜ ደርሳ ታሪክ በሰራችበት የ2022ቱ የኳታር ዓለም ዋንጫ ላይ ነበር። በጨዋታው ሞሮኮ 2ለ1 ማሸነፏ ይታወሳል። የዛሬው ተጠባቂ ጨዋታ ምሽት 2፡00 ላይ በሁስተን ስታዲየም ይጀምራ ል።
ፓራጓይ ከ ፈረንሳይ
ፈረንሳይ በርካቶች ለምን ዋንጫ ታሸንፋለች ብለው እንደገመቱ በትግባር እያሳየች ትገኛለች። የፊት መስመር ተጫዋቾቹ ኪሊያን ምባፔ ፣ ማይክል ኦሊሴ እና ኡስማን ዴምቤሌ የፈጠሩት ጥምረት ለየትኛውም ብሄራዊ ቡድን ተከላካይ ስጋት ነው።
በድጋሚ በሌላ ዓለም ዋንጫ እየደመቀ ሚገኘው ኪሊያን ምባፔ ከወዲሁ ስድስት ግቦችን አስቆጥሯል ፤ ኡስማን ዴምቤሌም አራት ግቦች በስሙ ተመዝግበዋል። የግብ እድል የመፍተር ሂደቱን በላቀ ደረጃ እየተወጣ የሚገኘው ማይክል ኦሊሴ አምስት ግብ የሆኑ ኳሶችን በማቀበል ተፅዕኖ ፈጣሪነቱን አሳይቷል።
ደረጃቸው ከፍ ያሉ የፊት መስመር ተጫዋቾችን የያዘችው ፈረንሳይ በዘንድሮ ውድድር ባደረገቻቸው አራት ጨዋታዎች ሦስት እና ከዚያ በላይ ግቦችን በማስቆጠር ነው ያሸነፈችው።
አብዛኛው ግምቶች ወደ ፈረንሳይ ቢያደሉም ፓራጓይ ቀላል ተጋጣሚ አትሆንም። ደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር ለዛሬው ጨዋታ የበቃችው የአራት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ጀርመንን በመለያ ምት አሸንፋ ነው።
ፓራጓይ በታሪኳ ለሁለተኛ ጊዜ ሩብ ፍፃሜ ለመግባት ሌላ ያልተጠበቀ ድል ፈረንሳይ ላይ ማስመዝገብ ይጠበቅባታል። ለሊት 6፡00 የሚጀምረው ጨዋታ ከ67 ሺ በላይ ተመልካቾችን በሚይዘው ፊላደልፊያ ስታዲየም ይከናወናል።
በሸዋንግዛው ግርማ