AMN – ሰኔ 23/2018 ዓ.ም
ባልተጠበቀ ሁኔታ ለሚደረግ የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ተጋላጭ ለሆኑ ሴቶች፣ ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል የሚያግዙ የድንገተኛ የወሊድ መቆጣጠሪያዎች ስላላቸው ፋይዳ እና አጠቃቀም በአበበች ጎበና እናቶችና ህጻናት ሆስፒታል የማህጸንና ጽንስ አሲስታንት ዶክተር አህመድ ባቡ ለኤ ኤም ኤን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የድንገተኛ የወሊድ መቆጣጠሪያ ማለት አንድ ሴት ባልታሰበ ወይም በድንገተኛ ሁኔታ በምታደርገው ግንኙነት ምክንያት እርግዝና እንዳይፈጠር ለመከላከል የሚያግዝ መንገድ ነው።
ይህ ዘዴ በአግባቡ እና በወቅቱ ጥቅም ላይ ሲውል እስከ 95 በመቶ የመከላከል አቅም አለው።
የድንገተኛ የወሊድ መቆጣጠሪያዎች ለድንገተኛ አጋጣሚዎች ብቻ የተዘጋጁ እንጂ በቋሚነት የምንጠቀምባቸው የወሊድ መቆጣጠሪያ መንገዶች አይደሉም።
ዶክተር አህመድ በተለይ ይህንን በተደጋጋሚ ለሚወስዱ ሴቶች ማስጠንቀቂያ ይሰጣሉ፡፡

ይህም ምንም እንኳን ውጤታማ ቢሆኑም፣ በተደጋጋሚ ሲወሰዱ ስኬታማ የመሆን እድላቸው ሊቀንስ ይችላል።
በተለይ ሚኒ ፒልስ የሚባለው እስከ 95 በመቶ የመከላከል አቅም ቢኖረውም አንዳንዴ ያለመሳካት እድል ኖሮት እርግዝና ከተፈጠረ ይህ እርግዝና ከማህፀን ውጭ የመሆን እድሉ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ፣ ለከፍተኛ ችግር ሊዳርግ ይችላል ይላሉ፡፡
ከትዳር በፊት የሚደረግ ግንኙነትን ማስወገድ የተሻለ ቢሆንም፣ የማይቀር ከሆነ ግን ለረጅም ጊዜ መከላከል የሚችሉ ቋሚ የወሊድ መቆጣጠሪያ መንገዶችን መጠቀም ተገቢ እንሆነ ይመክራሉ፡፡
የድንገተኛ የወሊድ መቆጣጠሪያ ውጤታማነቱ በመጀመሪያዎቹ 24 ሰዓታት ውስጥ ሲሰጥ በጣም ከፍተኛ ሲሆን፣ ቀኑ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ውጤታማነቱ እየቀነሰ ይሄዳል።
ቢበዛ ግንኙነት ከተደረገ በአምስተኛው ቀን ውስጥ መወሰድ አለበት ይላሉ።
ህብረተሰቡ በአብዛኛው የሚያውቀው “ፖስትፒል” የሚባለውን ቢሆንም፣ ሌሎች አማራጮችም አሉ የሚሉት ሐኪሙ፣ እነዚህም፤ (አይ ዩ ዲ) ማህፀን ላይ የሚቀመጥ ሲሆን እስከ 5ኛው ቀን ድረስ ጥቅም ላይ ከዋለ በጣም ውጤታማ ነው።

ሚኒ ፒልስ በተለምዶ 72 ሰዓት ፒልስ በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ እስከ 5 ቀን ድረስ ሊያገለግል ይችላል።
ኮምባይንድ ኦራል ኮንትራሴፕቲቭ መድኃኒቶቹ በማይገኙበት ጊዜ በሃኪም ትዕዛዝ እና ድጋፍ ሊወሰዱ ይችላሉ።
የድንገተኛ የወሊድ መቆጣጠሪያ፣ ያልታቀደ ወይም ድንገተኛ ግንኙነት ሲደርግ፣ በአስገድዶ መድፈር ምክንያት ግንኙነት ሲፈጸምባቸው፣ ቀደም ሲል ይጠቀሙ የነበሩት የወሊድ መቆጣጠሪያዎች ውጤታማነታቸው አጠራጣሪ ሲሆን ለሴቶች አስፈላጊ ናቸው፡፡
በፍሬሕይት ብርሃኑ