73ኛው የአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ትንበያ ፎረም በአዲስ አበባ ይካሄዳል

You are currently viewing 73ኛው የአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ትንበያ ፎረም በአዲስ አበባ ይካሄዳል

AMN- ግንቦት 10/2018 ዓ.ም

73ኛው የታላቁ የአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ትንበያ ፎረም (GHACOF 73) ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ ይጀመራል።

ፎረሙ የሚካሄደው “የአየር ንብረት አገልግሎቶች፤ ለአይበገሬነት እና ዘላቂ ልማት” በሚል መሪ ሀሳብ ነው።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የአየር ንብረት ትንበያ እና የመተግበሪያ ማዕከል(ICPAC) ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን ፎረሙን እንዳዘጋጀው ተገልጿል።

ስብሰባው ትንበያ ከመስጠት ባለፈ ትንበያዎቹን ወደ ተግባር መቀየር እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የቅድመ ማስጠንቀቂያና ቅድመ ዝግጅት እርምጃዎችን ማጠናከርን ያለመ ነው።

የአየር ንብረት መረጃዎች አርሶ አደሮች፣ የጤና ባለሙያዎችንና የአደጋ ስጋት አመራሮችን በቀጥታ እንዲደግፉ ማድረግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ምክክር እንደሚደረግ ኢጋድ አመልክቷል።

በብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ተቋማት መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር ሌላኛው የመወያያ አጀንዳ ነው።መድረኩ ለታላቁ የአፍሪካ ቀንድ ግብርና እና የውሃ ሀብት ወሳኝ የሆነውን ከእ.አ.አ ከጁን እስከ ሴፕቴምበር 2026 ያለውን የዝናብ ወቅት ትንበያ ይቀርብበታል።

ሚኒስትሮች፣ የምርምር ተቋማት፣ ሰብአዊ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ማህበራት እና የግል ባለሀብቶች ይሳተፋሉ። ይህ የተሳታፊዎች ስብጥር ሳይንስን ከፖሊሲ ጋር ለማገናኘት የታለመ ነው።

የአየር ንብረት መዛባት የሩቅ ስጋት መሆኑ ቀርቶ በደጃፋችን ላይ ያለ ተጨባጭ አደጋ ነው ያለው ኢጋድ፣ ፎረሙ በታላቁ የአፍሪካ ቀንድ የሚገኙ ማህበረሰቦች በቂ መረጃ እንዲኖራቸውና አስቀድመው ዝግጁ እንዲሆኑ ማስቻል ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን አመልክቷል።

በፎረሙ ማብቂያ የጋራ አቋም መግለጫ ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል። የጋራ መግለጫው በቀጣይ ለሚከናወኑ የቅድመ-ማስጠንቀቂያ ተግባራትና ለማህበረሰብ ጥንካሬ ግንባታ ስራዎች እንደ ዋና ግብዓት እንደሚያገለግል መመላከቱን ኢዜአ ዘግቧል።

ከዋናው መድረክ አስቀድሞ ከባለድርሻ አካላት ጋር የበይነ መረብ ውይይት እና የአየር ንብረት ትንበያ ልማት አውደ ጥናት ተደርጓል።

ቀጣናዊ ፎረሙ እስከ ነገ ይቆያል።

72ኛው የታላቁ የአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ትንበያ ፎረም (GHACOF 72) በጥር ወር 2018 ዓ.ም በኬንያ ናይሮቢ መካሄዱ የሚታወስ ነው።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review