AMN ግንቦት 11/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት መጠበቅ ያላትን የጎላ አስተዋጽኦ አጠናክራ ትቀጥላለች የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።
በምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል የቀድሞው ዳይሬክተር ኬንያዊው ብርጋዲዬር ጄኔራል ፖል ካሁሪያ ንጄማ እና በምትካቸው የተሾሙት ሩዋንዳዊው ብርጋዲዬር ጄኔራል ሮናልድ ርዊቫንጋ ከፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና ከመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ወቅትም የቀድሞው የተጠንቀቅ ኃይሉ ዳይሬክተር ኬንያዊ ብርጋዲዬር ጄኔራል ፖል ካሁሪያ ንጄማ በስራ ዘመናቸው ወቅት የነበረውን የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል የስራ እንቅስቃሴ የሚያሳይ አጭር ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በምን ዓይነት የሰላም እና ደህንነት ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ የተለያዩ ሀገራትን በመጥቀስ ያብራሩ ሲሆን ኢትዮጵያ ለእነዚህ የቀጠናው የሰላም እና ደህንነት ተግዳሮቶች መፈታት ላሳየችው ቁርጠኝነት፣ ከፍተኛ ድጋፍ ሰጭነትና ቀደም የመሪነት ሚና አድናቆታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በበኩላቸው የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ድርጅት የተመሰረተው የአባል ሀገራትን ጥምረት እና ፖለቲካዊ አንድነት ከፍ ለማድረግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይልን ጨምሮ ለአፍሪካ ሰላም እና ፀጥታ መስፈን ያበረከተችው እና እያበረከተችው የምትገኘው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህ በቀጠናው ሰላም እና የፀጥታ ጉዳዮች ላይ አወንታዊ ተፅዕኖ የማሳደር እንቅስቃሴና በተጠንቀቅ ኃይሉ ውስጥ ያላትን የጎላ ሚና በአግባቡ የመወጣት ሂደት ወደፊትም የበለጠ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ፊልድ ማርሻሉ አዲስ ወደ ስልጣን ለመጡት ሩዋንዳዊው የተጠንቀቅ ኃይሉ ዳይሬክተር ብርጋዲዬር ጄኔራል ሮናልድ ርዊቫንጋም መልካም የስራ ዘመን ምኞታቸውን ገልፀዋል፡፡
ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በቀጣናው ላይ ያሉትን የሰላም እና የደህንነት ችግሮች ለመፍታት ያደረገችው ጥረት ከፍተኛ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በቀጣይም ለዓለም፣ ለአፍሪካ እና ለቀጣናው ሰላም የምታበረክተውን አስተዋፅኦ ከአጋር አካላት ጋር በተናበበ እና በተደራጀ መልኩ ከመቼውም ጊዜ በላይ አጠናክራ የምትቀጥል መሆኗን አንስተዋል፡፡
የአባል ሀገራትን ስሜት ጠብቆ እና ከድጋፍ ሰጭ ባለድርሻ አካላት ጋር ተግባብቶ ይህን የፀጥታ ተቋም መምራት ታላቅ የሃላፊነት ደረጃ በመሆኑ ተሰናባቹ ጀኔራል ዳይሬክተር የተጠንቀቅ ኃይሉን በመምራት ለተጫወቱት ሚና ሚኒስትሯ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
አዲሱ ዳይሬክተር ብርጋዲዬር ጄኔራል ሮናልድ ርዊቫንጋም ኢትዮጵያ የቀደመውን ጉልህ ሚናዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
እሳቸውም ከአባል እና ከአጋር አካላት ጋር በትብብር በመስራት የራሳቸውን አሻራ ለማስቀመጥ እንደሚሰሩ መናገራቸውን ከመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።