ከቅድመ መደበኛ የተጀመረው የአዲስ አበባ ከተማ የትውልድ ግንባታ መሠረት

AMN – ግንቦት 17/2018 ዓ.ም

ባለፉት አምስት ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ የተመዘገቡ የልማት ስኬቶች ሲነሱ፣ የኮሪደር ልማቱና የከተማዋ ገፅታ መቀየር ቀዳሚውን ስፍራ ይይዙ ይሆናል።

ሆኖም ግን ከእነዚህ አስደማሚ መሠረተ-ልማቶች ጀርባ፣ በከተማዋ የረጅም ጊዜ ዕጣ ፈንታ ላይ ትልቅ አሻራ የሚያስቀምጥ ሌላ የስኬት ምዕራፍ እየተከናወነ ይገኛል፤ እርሱም የቅድመ መደበኛ ትምህርት ትግበራና ፍትሐዊነት ነው።

የከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ጥራትን ከመሠረቱ ለመገንባት በሚል ባለፉት አምስት ዓመታት በቅድመ መደበኛ ዘርፍ ላይ ያደረገው ከፍተኛ መዋዕለ-ንዋይ፣ በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የትምህርት ሥርዓት ላይ መዋቅራዊ ለውጥ እያስገኘ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ሪፖርቶችና መረጃዎች ያመለክታሉ።

ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ከተማ ልጆችን መዋለ ሕፃናት መላክ የአቅም ማሳያና የከፍተኛ ገቢ ያላቸው ወላጆች መብት ብቻ ተደርጎ ይወሰድ ነበር። አቅም የሌላቸው ወላጆች ልጆች ያለምንም የቅድመ መደበኛ ዝግጅት በቀጥታ አንደኛ ክፍል እንዲገቡ መገደዳቸው፣ በትምህርት ጥራትና በተማሪዎች ውጤታማነት ላይ የጎላ የፍትሐዊነት መጓደል ፈጥሮ ቆይቷል።

ይህንን ክፍተት ለመሙላት የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት አምስት ዓመታት የወሰዳቸው እርምጃዎች ውጤት ማሳየት መጀመራቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይህንን እውነታ በተመለከተ፣ ቀደም ሲል አቅም ያለው ወላጅ ብቻ ልጁን መዋለ ሕፃናት እየላከ አቅም የሌለው ደግሞ በቀጥታ አንደኛ ክፍል ያስገባ ነበር፤ ይህ የፍትሐዊነት መጓደል ነው። አሁን ግን በመንግሥት ደረጃቸውን የጠበቁ መዋለ ሕፃናትን በመገንባት፣ የደሃው ልጅም እንደ ሀብታሙ ልጅ እኩል የመማር ዕድል እንዲያገኝ አድርገናል ብለዋል።

ይህ የፖሊሲ ለውጥ በንግግር ብቻ የተገደበ ሳይሆን መሬት ላይ በወረዱ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የተደገፈ መሆኑን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ዓመታዊ የስታቲስቲክስ መረጃዎች ያረጋግጣሉ።

ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች እና በኮንዶሚኒየም መንደሮች ውስጥ ደረጃቸውን የጠበቁ፣ ማራኪና ሙሉ የሕፃናት መጫወቻ ያካተቱ በርካታ አዳዲስ ዘመናዊ የመንግሥት መዋለ ሕፃናት ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል።

በተጨማሪም በከተማዋ በሚገኙ በሺዎች በሚቆጠሩ የመንግሥት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የቅድመ መደበኛ ወይም የ”ዜሮ” ክፍሎች ተደራጅተው ከመደበኛው የትምህርት ሥርዓት ጋር እንዲቀናጁ ተደርጓል። ይህም ከመቶ ሺህ በላይ ሕፃናትን በነፃ የማስተናገድ አቅም ፈጥሯል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅና የትምህርት አሰጣጡን ከማዘመን ባለፈ፣ የተማሪዎችን ሁለንተናዊ አእምሯዊና አካላዊ ዕድገት ማዕከል ያደረጉ ሥራዎችንም አከናውኗል።

በዚህም በቅድመ መደበኛና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተጀመረው የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ትልቁን ድርሻ ይይዛል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፕሮግራሙ በትምህርት ጥራት ላይ ያለውን አወንታዊ ተፅዕኖ በተመለከተ፣ “የትምህርት ጥራት የሚጀምረው ተማሪው በክፍል ውስጥ ቁጭ ብሎ ለመማር ካለው ዝግጁነትና ምቾት ነው። ተርቦ የሚማር ሕፃን የትምህርት ጥራትን ሊያረጋግጥ አይችልም። በመሆኑም የትምህርት ቤቶች ምገባ ፕሮግራማችንን ከቅድመ መደበኛ ጀምረን በቁርጠኝነት የምንሠራው ለዚህ ነው” በማለት የስትራቴጂውን አስፈላጊነት አስምረውበታል።

ይህ አሠራር ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ እንዲቆዩና የመማር ማስተማር ሂደቱን ሙሉ ትኩረት ሰጥተው እንዲከታተሉ በማድረግ ረገድ በተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መረጃ ፈንድ (UNICEF) ሳይቀር ከፍተኛ አድናቆትን ያተረፈ ምርጥ ተሞክሮ ሆኖ ቀርቧል።

የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት መምህራንን በሕፃናት ሥነ-ልቦና ማሰልጠን፣ የትምህርት ቁሳቁሶችን ማሟላትና ነፃ የደንብ ልብስና ደብተር ማቅረብ መቻሉ ከተማዋ ለነገው ትውልድ የጣለችውን ጠንካራ መሠረት ያሳያል።

“እኛ የምንገነባው ትውልድ ነው፤ ትውልድ ደግሞ የሚገነባው ከመሠረቱ ነው” የሚለው የከንቲባ አዳነች አቤቤ ንግግር አስተዳደሩ ለትውልድ ግንባታ ያለውን የ ፀና አላማ በግልፅ የሚያሳይ ነው፡፡

አዲስ አበባ ዛሬ በቅድመ መደበኛ ሕፃናቶቿ ላይ እየዘራችው ያለው እውቀት፣ ፍትሐዊነትና እንክብካቤ፣ ነገ አገሪቱን የሚረከቡ ብቁ፣ ሥነ-ምግባር ያላቸውና በሳይንስ የተደገፉ ዜጎችን ለማፍራት የተጣለ የማይናወጥ መሠረት መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይስማሙበታል።

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review