ህጻናት ፣ ወጣቶች እና ሴቶችን ያስቀደመ ልማት

AMN – ግንቦት19/2018 ዓ.ም

ዜጎች ህይወት ላይ የሚመጣ ተጨባጭ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ የአንድን ከተማ ወይንም ሀገር እውነተኛ ዕድገት ያመላክታል፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ ህጻናትን፣ ወጣቶችን እና ሴቶችን በአንድ ጠንካራ የለውጥ ሰንሰለት በማስተሳሰር የማህበረሰቡን የዕለት ተዕለት ህይወት የሚያሻሽል እና ማህበራዊ ፍትህን የሚያረጋግጥ በርካታ ሥራዎችን ሰርቷል፡፡

ከየትኛውም የልማት ሥራ በፊት የነገዋን ከተማ የሚረከበውን ትውልድ ማዳን እና ማብቃት በለውጡ መንግሥት ቅድሚያ ተሰጥቶታል።

አቅም ማነስ የህጻናትን የመማር መብት እንዳይነጥቅ፣ አስተዳደሩ የትምህርት ቤት የምገባ መርኃ-ግብርን በስኬት እየመራ ይገኛል።

በ2011 ዓ.ም የተጀመረው የተማሪዎች የምገባ መርኃ-ግብር በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ባሉ በሁሉም የመንግስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለሚማሩ ከ779 ሺህ በላይ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ ይመገባሉ።

በዚህም ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሴቶች የሥራ እድልን መፍጠሩን የከንባቲ ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

እንዲሁም ተማሪዎች የትምህርት ቤት ዩኒፎርም፣ ደብተርና ቦርሳ በነፃ እንዲያገኙ ተደርጓል። ይህ የተማዎች የምገባ መርኃ-ግብር እና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ፤ በምግብ እጥረት ምክንያት ተማሪዎች ከትምህርት ቤት እንዳቀሩ ከማድረግ ባለፈ የተማሪዎችን ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

በተጨማሪም በአፍሪካ ደረጃ አርዓያ የሆነው የቀዳማይ ልጅነት ልማት መርኃ-ግብር ፤ ልጆች በዕድላቸዉ ሳይሆን በእንክብካቤ ያድጋሉ በማለት ዕድሜያቸው ከ6 ዓመት በታች የሆኑ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ህጻናት ሁሉን አቀፍ አገልግሎት እያገኙ ነው፡፡

ለዚህም ስኬት በከተማዋ ሕፃናት ቦርቀው የሚጫወቱባቸው ከ5 ሺህ በላይ የልጆች መጫወቻ ስፍራዎችና እንክብካቤ የሚያገኙባቸው ከ1 ሺህ በላይ ማቆያ (ዴይኬር) ማዕከላት ተገንብተዋል።

እንዲሁም የከተማዋ ወጣቶች የሥራ ዕድል ጠባቂ ከመሆን ወጥተው የሥራ ፈጣሪነት ክህሎት እንዲላበሱ በኮዲንግ፣ በሶፍትዌር ማበልጸግ እና በተለያዩ ዘርፎች እየሰለጠኑ ይገኛሉ።

በከተማዋ የብቃት የሥራ ልምምድ መርኃ ግብር ከተጀመረበት 2014 ዓ.ም ጀምሮ ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 25 ያሉ 49 ሺህ የሚሆኑ ወጣቶች የሥራ እና የዲጂታል ክህሎት ስልጠና ወስደው በተፈጠረላቸው ትስስር የሥራ ባለቤትነት እና አምራች ሆነዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፤ በመጋቢት 2018 ዓ.ም በምግብ ዋስትና እና ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም 15 ሺህ 492 ተጠቃሚዎችን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በማሸጋገር አስመርቀዋል፡፡

በተጨማሪም ክህሎት እና የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች በካፒታል እጥረት እንዳይሰናከሉ በርካታ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን በሳለፍነው ወር ብቻ ለ1 ሺህ 278 ኢንተርፕራይዞች የመስሪያ ቦታ ሼዶችን ተላልፈዋል። በዚህም 3 ሺህ 889 አንቀሳቃሾችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ፤ ሴቶችን በኢኮኖሚ እና በስነ-ልቦና ማብቃት መላውን ማህበረሰብ መለወጥ ነው በሚል እሳቤ ጥልቅ የሆኑ ማህበራዊ ችግሮችን የሚፈቱ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ተግብሯል።

ለአብነትም ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ተንብቷል፡፡ማዕከሉ የተሻለ ነገን፣ ብሩህ ተስፋን፣ ፅናትና የሰርቶ የመለወጥ እድልን የመትከል ማሳያ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ማዕከሉን በተመረቀበት ወቅት ገልጸዋል።

በጎዳና ላይ እና በከባድ የህይወት ፈተና ውስጥ የነበሩ ሴቶችንና እናቶችን በማንሳት፤ የህክምና፣ የስነ-ልቦና እና የሙያ ስልጠና በመስጠት ወደ አምራችነት የሚቀይር ትልቅ የተስፋ ማዕከል ሆኗል። በዚህም ሴቶች በማዕከሉ ሰልጥነው ከራሳቸው አልፈው ለብዙዎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡

እንዲሁም እናቶች የህጻናት ማቆያ በማጣት ከቤት እንዳይቀሩ ከ5 ሺህ በላይ እናቶች ስልጠና ወስደው በሰፈራቸው ልጆችን በማሳደግ እንዲሰማሩ ተደርጓል፡፡

በአጠቃላይ አዲስ አበባ አስተዳር በላፉት የለውጥ አመታት ከህጻናት ተማሪዎች ባሻገር በሴፍትኔት ፕሮግራም ውስጥ ተይዘው ሲረዱ የነበሩ ከ695 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በማሸጋገር ራሳቸውን እንዲችሉና ቤተሰቦቻቸውን እንዲደግፉ ተደርጓል።

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review