AMN-ሰኔ 9/2018 ዓ.ም

4ኛው ዓለም አቀፍ የሳይበር ደኅንነት ኮንፈረንስ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ሳይበር ደኅንነት አሶሴሽን እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እንዲሁም ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት በጋራ በመሆን ኮንፈረንሱን እንደሚያዘጋጁት ተገልጿል፡፡
ኮንፈረንሱ በመጭዉ ሰኔ 17 እና 18/2018 ዓ.ም በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ የሚካሄድ ሲሆን የአፍሪካ፣ አውሮፓ፣ አሜሪካ እና የተለያዩ አገራት መሪዎችና ባለሙያዎች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች እና ከ10 በላይ የፓናል ዉይይቶችም ይካሄዳሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በኤ አይ ወይም በሰዉ ሰራሽ አስተዉሎት ምክንያት የሳይበር ደኅንነት ስጋት እየጨመረ በመምጣቱ ኮንፈረንሱን ለማድረግ አስፈላጊ ሆኗል ያሉት የኢትዮጵያ ሳይበር ደኅንነት አሶሴሽን ፕሬዝዳንት ብርሃኔ በየነ (ዶ/ር) ናቸዉ፡፡

በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የዲጂታልና ኢንፎርማሽን ቴክኖሎጂ ዋና ኃላፊ የሆኑት አሞስ ሆሞድዛ በበኩላቸው፤ ኤ አይ በርካታ የፈጠራ እድገትን ያመጣ ቢሆንም በሳይበር ደኅንነት ላይ ከፍተኛ የሆነ አደጋን ደቅኗል ብለዋል፡፡
ዓለም አቀፉ የሳይበር ደኅንነት ኮንፈርንስ በዚህ አመት ለ4ኛ ጊዜ የሚደረግ ሲሆን ኢትዮጵያ ይህንን ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ለ2ኛ ጊዜ ነው የምታስተናግደው፡፡
በየሺዋስ ዋለ