AMN- ግንቦት 19/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ እና ዘመናዊ የኮሪደርና የከተማ ልማት ሪፎርሞች የከተማዋን ገጽታ ሙሉ በሙሉ በመቀየር ረገድ ስኬታማ ውጤት አስመዝግበዋል።
ቀደም ሲል ከተማዋን የማይመጥኑ፣ ጽዱ እና ውብ ያልነበሩ በርካታ አካባቢዎች ዛሬ ላይ ተለውጠው ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ማራኪና ተስማሚ ሆነዋል።ይህ ሰፊ የልማት እንቅስቃሴ መዲናዋን ከማስዋብ ባለፈ የኢኮኖሚ፣ የቱሪዝምና የማህበራዊ ትስስር ማዕከል አድርጎታል።
የከተማዋ የልማት ሪፎርም የነዋሪዎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እና ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን መሠረት ያደረገ ሲሆን ከመኪና መንገዶች ጎን ለጎን የተገነቡት ዘመናዊ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶች የትራፊክ ፍሰት ከማቃለላቸው ባለፈ ነዋሪዎች በነጻነትና በደኅንነት እንዲንቀሳቀሱ አስችለዋል።

እንዲሁም ቀደም ሲል የተረሱና የተበከሉ የነበሩ የወንዝ ዳርቻዎች ፤በወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች ወደ አረንጓዴ ስፍራዎችና የቱሪስት መዳረሻነት ከመቀየር ባለፍ የነዋሪዎችን የጎርፍ ስጋት መቀነሳቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ በርካታ ዘመናዊ ፓርኮች፣ የህዝብ መዝናኛዎች እና ግዙፍ ሁለገብ የገበያ ማዕከላት ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
በተለይም አዲስ አበባን የአፍሪካ ብሎም የዓለም የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በተሰራው ስራ፤ ከተማዋ ትላልቅ የጎዳና ላይ በዓላትን፣ አውደርዕይ እና ባህላዊ ትዕይንቶችን በደማቅ ሁኔታ ማስተናገድ የምትችልበት አቅም ተፈጥሯል።

ባለፉት አምስት አመታት በከተማዋ ከ60 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች የተገነቡ ሲሆን ፤ ከእነዚህም ውስጥ የከተማዋን ባህላዊና ሃይማኖታዊ ብዝሃነት በሚያሳይ መልኩ የተነደፉ ፕሮጀክቶች ተካተዋል።
የለውጡ መንግስት የከተማዋን ነዋሪዎች ፍላጎትና የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማትን ያካተተ የልማት አቅጣጫን ተከትሏል። ይህ አካታችነት አቅጣጫ በተለይ በሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓቶች ላይ በግልጽ ተተግብሯል፡፡

ለአብነትም ፤ የእስልምና እምነት ተከታዮች የረመዳን ወር የጎዳና ላይ ኢፍጣር እና የተለያዩ የሶላት ስነ-ስርዓቶችን በሰላም እና በነጻነት የሚያከናውኑባቸው ስፍራዎች ይበልጥ ምቹ፣ ውብ እና ማራኪ ሆነው ተዘጋጅተዋል።
የመስቀል በዓልን በደመቀ ስነ ሥርዓት ለማክበርም የመስቀል አደባባይ ከመቼውም ጊዜ በላይ ምቹ ሆኖ ተሰርቷል።
ይህም አዲስ አበባ የሁሉም እምነቶችና ብሔር ብሔረሰቦች መከባበርና እኩልነት የሚንጸባረቅባት፣ የአብሮነት ተምሳሌት መሆኗን በተግባር አረጋግጧል፡፡
በትዝታ መንግስቱ