በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ህብረተሰቡ በጊዜ ወጥቶ ድምጹን እንዲሰጥ ነዋሪዎች ጥሪ አቀረቡ

AMN- ግንቦት 23/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ከፍተኛ መራጮች የተመዘገቡበት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ፤ ፍትሃዊ እና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ በጊዜ ወጥቶ ድምጹን እንዲሰጥ የአዲስ ከበባ ከተማ ነዋሪዎች ጥሪ አቅርበዋል።

ነገ በጊዜ ወጥተው ድምፃቸውን ለመስጠትም ዝግጁ መሆናቸውን ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ቱጁባ አዩ፣ አንተነህ እውነቱ እና አበራ ንጋኒ ከነ ቤተሰቦቻቸው ማለዳ በመውጣት ድምፃቸውን ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አየለ ሌራ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያን ሊያስተዳድራት የሚችለውን መንግስት በመምረጥ የድርሻዬን እወጣለሁ ብለዋል።

ድምፃቸው የነገ መፃዒ ዕጣ ፋንታቸውን የሚወስኑበት መሆኑን የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ ይህ አጋጣሚ ፈጽሞ መባከን እንደሌለበትም አስረድተዋል።

ሁሉም በማለዳ በመነሳት በንቃት ድምጹን መስጠት እንደሚገባው በማንሳትም፤ ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ እና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲከናወን ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review