ፌዴራል ፖሊስ የታጣቀቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች የምርጫ ሂደቱን ውጤታማነት በማስጠበቅ ረገድ ገንቢ ሚና ተጫውተዋል

AMN- ግንቦት 25 /2018 ዓ/ም

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የታጣቀቸው ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሰባተኛው ጠቅላላ የምርጫ ሂደትን ውጤታማነት በማስጠበቅ ረገድ ገንቢ ሚና መጫወታቸውን ገለጸ።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት በትላንትናው እለት ተካሂዷል።

በዚህም ኢትዮጵያዊያን መርጠዋል፤ ኢትዮጵያም አሸንፋለች።

የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ፍጹም ሰላማዊ ፣ ዲሞክራሲያዊ እና ገለልተኝነቱን ጠብቆ እንዲካሄድ የፌዴራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ከፍተኛ ስራ ሰርቷል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የቴክኖሎጂ ማስፋፍያ መምሪያ ሃላፊ ኮማንደር ደምሴ ይልማ እንደገለጹት፤ ተቋሙ በምርጫው ወቅት ዜጎች በነጻነት ድምጻቸውን የሚሰጡበትን ሂደት ለማገዝ ሰፊ ዝግጅት አድርጓል።

በተለይም በአዳዲስና ፈጣን እድገት ላይ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን ከነባሮቹ የቴክኖሎጂ መሰረተ-ልማቶች ጋር በማቀናጀት፣ የፖሊስ ሰራዊት ስምሪት እና የምርጫ ጣቢያዎችን እንቅስቃሴ እያንዳንዱን በቀጥታ ለመከታተል መቻሉን ገልጸዋል።

በዚህም በየአካባቢው የሚታየውን የፀጥታ ሁኔታና የምርጫ ድባብ አመራሩ ከኮማንድ ኮንትሮል ማዕከል ሲከታተል መቆየቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከሁሉም የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በሰራው ስራ የምርጫው ሂደት ሰላማዊ እና ውጤታማ በሆነ መንገድ መከናወኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

See less

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review