ኢትዮጵያ እና ፊንላንድ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋገጡ

You are currently viewing ኢትዮጵያ እና ፊንላንድ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋገጡ

AMN ግንቦት 26/2018

ኢትዮጵያ እና ፊንላንድ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓና አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር መለስ ዓለም (ዶ/ር) ከፊንላንድ ልዑክ ጋር ምክክር አድርገዋል።

ሀገራቱ በካሄዱት የፖለቲካ ምክክር መድረክ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ ባህል እንዲሁም ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ትብብራቸውን ይበልጥ ለማሳደግ የሚያስችላቸውን ውይይት አካሂደዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓና አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር መለስ ዓለም (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት፣ በፈጠራና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፎች የሀገራቱን ትብብር ለማስፋት የሚያስችል ከፍተኛ አቅም አላት ብለዋል።

ኢትዮጵያ ባካሄደችው የሪፎርም ሥራዎች፣ እያደገ የመጣው የሀገር ውስጥ ገበያ፣ ሰፊ የሰው ኃይል እና ቁርጠኛ መንግሥትበአፍሪካ ቀዳሚ የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗንም ጠቅሰዋል።

የፊንላንድ ባለኃብቶችም በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መሰማራት የሚችሉበት ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች መኖራቸውንም አብራርተዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው አጋርነት በሁሉም መስክ ውጤታማና ወደላቀ ደረጃ የተሸጋገረ እንዲሆን ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት እንደምትሰራም አምባሳደር መለስ አረጋግጠዋል።

መሰል ምክክሮች በሀገራቱ መካከል ያለውን ትብብርና ግንኙነት ይበልጥ ለማስፋት ምቹ ምህዳር የሚፈጥር በመሆኑም ሊጠናከር እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ የቀድሞ የፊንላንድ አምባሳደርና የልዑኩ መሪ ኦቲ ሆሎፔይኔን በዚሁ ወቅት፤ እንዳሉት፤ ፊንላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት እያደገ መሆኑን ተናግርዋል።

የሁለትዮሽ ትብብራችን ወደ ጠንካራ አጋርነት እና ወደ ላቀ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እየተሸጋገረ ነው ያሉት የልዑኩ መሪ ሀገራቱ በንግድ እና የኢኮኖሚ ያላቸው ትብብር ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተሸጋገረ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት፣ በትምህርት፣ አካባቢና አየር ንብረት ለውጠ ዙሪያ፣ በባለብዙ ወገን ትብብርን፣ ሰላምን ጨምሮ በብዙ ዘርፎች ለፊንላንድ ቁልፍ አጋር መሆኗን‎ መናገራቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋትን እንዲሰፍን እንዲሁም ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሳለጥ እየተጫወተች ያለው ወሳኝ ሚና የሚደነቅ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የምታከናውናቸው ተግባራት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ፊንላንድ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግም አረጋግጠዋል።

በቀጣይም የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ እና በጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ፊንላንድ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ በቅርበት ለመሥራት ቁርጠኛ ናት ብለዋል።

ኢትዮጵያና ፊንላንድ ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት እንደ አውሮፓዊያን የዘመን ቀመር ከ1959 ጀምሮ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review