ከቆሻሻ ማከማቻነት ወደ አረንጓዴ ገነት፡ የአዲስ አበባ ወንዞች አዲስ ሕይወት

You are currently viewing ከቆሻሻ ማከማቻነት ወደ አረንጓዴ ገነት፡ የአዲስ አበባ ወንዞች አዲስ ሕይወት

AMN- ግንቦት 27/2018 ዓ.ም

ለዘመናት የአዲስ አበባ ወንዞች ሲነሱ በነዋሪው አእምሮ ውስጥ የሚቀረጸው ምስል ግልጽ ነበር፤ የፍሳሽ ቆሻሻ ማከማቻነት፣ የከረፋ ሽታ፣ እና የክረምት መግቢያ የጎርፍ ስጋት ነበር።

ከተማዋ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከልና የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ብትሆንም፣ በየሰፈሩ የሚፈሱት ወንዞቿ ግን ለነዋሪዎቿ የጤና ጠንቅና የአደጋ ምንጭ ሆነው ኖረዋል።

ዛሬ ግን ያ ታሪክ ተቀይሯል፤ የተማዋ ጀርባ የነበሩት ወንዞች ፊታቸውን ወደ ነዋሪው አዙረው የውበትና የልማት ምንጭ መሆን ጀምረዋል።

ይህንን ታላቅ ለውጥ በአካል ለመመስከር በቅርቡ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነውን የ22.25 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የቁርጥሚ ወንዝ ዳርቻ ልማትን መመልከት በቂ ነው።

በአንድ ወቅት ማንም ሊጠጋው የማይፈልገው ይህ ስፍራ፣ ዛሬ 5 ዘመናዊ አንፊ ቴአትሮችን፣ የሕፃናትና የአዋቂዎች ስፖርት ማዘውተሪያዎችን እና ማራኪ የሕዝብ መዝናኛዎችን አካቶ የከተማዋ አዲስ የቱሪስት መዳረሻ ሆኗል።

በተመሳሳይ መልኩ፣ በያዝነው ሳምንት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና በከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመረቀው የ597 ሄክታር ስፋትና 9.6 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የእንጦጦ ቀጨኔ የወንዝ ዳርቻ ልማት፤ የኢትዮጵያውያንን የመስራትና የመለወጥ አቅም ለዓለም ያሳየ ሌላው አስደናቂ ማሳያ ነው።

በአሁኑ ወቅት በሂደት ላይ የሚገኘው የቀበና ወንዝ ተፋሰስ ልማትም የወንዙን ተፈጥሯዊ ሥነ ምህዳር መልሶ በማደስ የአካባቢውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ በመቀየር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

በከተማዋ ለኑሮ ምቹ ያልሆኑ፣ ለአደጋ የተጋለጡ እና የተጎሳቆሉ አካባቢዎችን መልሶ በማልማት ዳግም ለነዋሪዎች ከፍተኛ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎችን እያስገኙ ይገኛሉ፡፡

በዚህም ከዚህ በፊት በክረምት ወቅት በከፍተኛ የጎርፍ አደጋ እና በንብረት ውድመት ስጋት ውስጥ የነበሩት የወንዝ ዳር ነዋሪዎች፣ በልማቱ አስተማማኝ እፎይታ እንዳገኙ መናገራቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

በወንዝ ዳርቻ የልማት ሥራ የተገነቡት የጎርፍ አደጋ መከላከያ ግንቦች የጎርፍ አቅጣጫን በመቆጣጠር እና የወንዞቹን መውረጃ መስመር በማስፋት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

ይህም በአካባቢው ይከሰት የነበረውን የህይወትና የንብረት አደጋ በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ አስችሏል፡፡

በመሰረተ ልማት እጦት በወንዞች ተለያይተው የቆዩ ሰፈሮች አሁን በተገነቡት አዳዲስ የእግረኛ እና የተሽከርካሪ ድልድዮች አማካኝነት መገናኘት ችለዋል፡፡

ድልድዮቹ ለህጻናትና አረጋውያን ደህንነት የተጠበቀ ከመሆኑም በላይ ማህበረሰቡ ርቀው የሚገኙትን የትምህርት፣ የጤና እና የእምነት ተቋማትን ያለ እንግልት በቀላሉ እንዲያገኝ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡

ሸማቾችና ነጋዴዎችም በቀላሉ ወንዞቹን ተሻግረው መገበያየት በመቻላቸው ለአነስተኛና መካከለኛ ንግዶች ሰፊ የገበያ ትስስር መፍጠርም ተችሏል፡፡

በአዲስ አበባ እየተተገበሩ ያሉ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች የከተማዋን ገጽታ በመለወጥ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ሲሆን ፕሮጀክቶቹ ከተማዋን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ከማድረጋቸውም ባለፈ፣ የነዋሪዎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review