AMN- ግንቦት 30/2018
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አዲስ አበባ የስፖርታዊ ሁነቶች መናገሻ ሆናለች፡፡ በመዲናዋ የሚካሄዱ ስፖርቶች በዓይነትም በብዛትም ቁጥራቸው እየጨመረ ይገኛል፡፡
በከተማዋ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማካሄድም እጅግ እየተለመደ መጥቷል፡፡
ከተማዋ ከቀድሞ በተለየ ለስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ተመራጭ እንድትሆን በከተማዋ የተገነቡት መሠረተ ልማቶች ወሳኝ ሚና አላቸው፡፡
በጥቂት ዓመታት ውስጥ በአስገራሚ ፍጥነት እንደ አዲስ ስፖርት ፓርክ ከመሰለው ግዙፍ የስፖርት ማዕከል እስክ በየሰፈሩ እየተገነቡ እስካሉት አነስተኛና መካከለኛ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ለአገልግሎት በቅተዋል፡፡

የዓድዋ ድል መታሰቢያም እንደ ቦክስ ፣ ቅርጫት ኳስ ፣ መርብ ኳስ እና እጅ ኳስ ለመሳሰሉት በቤት ውስጥ ሊከናዎኑ የሚችሉ ስፖርቶች ምቹ የመወዳደሪያ ዓውድ ፍጥሯል፡፡
የተዘጋጁት የስፖርት ማዘውተሪያዎች ከከተማዋ የኮሪደር ልማት ጋር ተዳምሮ አዲስ አበባን ከሐገር እስከ ዓለም አቀፍ ለሚዘጋጁ ስፖርታዊ ፉክክሮች ምቹና ተመራጭ እንድትሆን አድርጓታል፡፡
በቅርብ የተካሄዱት የአዲስ ግራንድ ፕሪ ዓለም አቀፍ ሩጫ ፣ ሲቲ ማውንቴን ባይክ ኤሊሚኔተር ፕሮ ሊግ ፣ የዞን 5 የምስራቅ አፍሪካ የዓለም አቀፍ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ትሮፊ የመሳሰሉት ዓለም አቀፍ ውድድሮች የመዲናዋን ተመራጭነት እና ለተለያዩ ስፖርቶች ምቹ መሆኗን አመላካች ናቸው፡፡
የሐገር ውስጥምየተለያዩ ስፖርታዊ ክንውኖችንም በተሸለ ሁኔታ እያስተናገደች ትገኛለች፡፡ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓድዋ ድል መታሰቢያ የተካሄደው የሚክስድ ማርሻል አርት በስፖርቱ የተፈጠረውን መነቃቃት የሚያሳይ ነው፡፡

በርካታ ስፖርታዊ ውድድሮች በመዲናዋ መካሄዳቸው ከጨዋታው ባለፈ ለሀገር ገጽታና ለኢኮኖሚ ከፍተኛ ፋይዳ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡
በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ ሁለንተናዊ የስፖርት ልማት ስራዎች በወጣቶች ሁለንተናዊ ዕድገት አወንታዊ ሚና ያላቸው ናቸው፡፡
ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በመገንባት ተተኪ ስፖርተኞች በብዛትና በጥራት ማፍራት የሚቻልባቸው ሁኔታዎች በእጅጉ ተመቻችተዋል፡፡
በየአካባቢው በተገነቡ ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያዎች እና በኮሪደር ልማቱ አማካኝነት አዲስ አበባ ውብና ጽዱ መዲና ብቻ ሳትሆን፣ በስፖርት የዳበረ ጤናማ ትውልድ የሚፈራባት ጤናማ ከተማ እየሆነች ትገኛለች።
በታደሰ ሽፈራው