የበለጸገችና ያደገች ኢትዮጵያን በጋራ ለማየትና ለትውልድ ለማውረስ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት እንዲቆሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ

AMN- ሰኔ 8/2018 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተባበረ ክንድ ድህነት ለመስበር፣ የጠለሸ ማንነት ለመቀየር፣ የበለጸገችና ያደገች ኢትዮጵያን በጋራ ለማየትና ለትውልድ ለማውረስ በአንድነት እንዲቆም፣ እንዲተባበር እና እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት ግዙፉን የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ የሥራ ሂደት በጎበኙበት ወቅት ነው፡፡

የቢሾፍቱ ኤርፖርት ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ ክብር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ብዙዎች አትችሉም የሚል ምልከታ ያለው እሳቤ ሲያራግቡ እንደሚሰማ አንስተዋል፡፡

ሆኖም ፈተናዎች በቅርበት እየፈታን ፕሮጀክቱን በታቀደለት ጊዜ በማጠናቀቅ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን አፍሪካ ማሰብ፣ ማቀድ፣ መስራት እና ማሳካት እንደምትችል ለዓለም የምናሳይበት አፍሪካን የምናነቃቃበት ግዙፍ ሥራ ነው ብለዋል፡፡

ለልጆቻችን የሚተርፍ ትልቅ መሰረት እዚህ ቦታ እያስቀመጥን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህ መሠረት የኢትዮጵያን ገጽ፣ የኢትዮጵያን መልክ እና የኢትዮጵያን ሀብት የሚቀይር ሥራ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ይህ ጊዜ የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ጊዜ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ጊዜው የእኛ መሆኑን መናገር ብቻ ሳይሆን፣ ያንን ለመተርጎም የሚያስችል ሥራ መስራት እንደሚያፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

ይህ ግዙፍ ሥራ እንዲከናወን በቅርበት የሚመሩ፣ የሚከታተሉ እና የሚደግፉ አካላትን ያመሰገኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከሁሉ በላይ መኖሪያቸውንም፣ የእርሻ ቦታቸውንም ለቀው ቦታው ለሀገር ልማት እንዲውል ላደረጉት በአካባቢው ለሚገኙ አርሶ አደሮች ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

አክለውም፣ ማንም አርሶ አደር በዚህ ፕሮጀክት ምክንያት የሚጎዳ አይኖርም ያሉ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ ለአካባቢው አርሶ አደሮች ብሎም ለኢትዮጵያና ለምስራቅ አፍሪካ ትልቅ በረከት ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተባበረ ክንድ የኢትዮጵያን ደህንነት ለመስበር፣ የጠለሸ ማንነትን ለመቀየር፣ የበለጸገችና ያደገች ኢትዮጵያን በጋራ ለማየት እና ለልጆቻችን ለማውረስ አንድ ላይ እንቁም፣ እንተባበር፣ እንስራ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review