የአዲስ አበባ የክረምት በጎ ፈቃድ ተግባር የከተማዋን ገጽታ እና የነዋሪውን ትስስር የለወጠ ነው

You are currently viewing የአዲስ አበባ የክረምት በጎ ፈቃድ ተግባር የከተማዋን ገጽታ እና የነዋሪውን ትስስር የለወጠ ነው

AMN- ሰኔ 9/2018 ዓ.ም

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በአዲስ አበባ ተግባራዊ እየሆነ ያለው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ ከቁሳዊ ድጋፍ ባለፈ የሰውን አቅም የመገንባትና የባለቤትነት ስሜትን የማሳደግ ትልቅ አቅም መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ ነው።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚተገበሩት የበጎ አድራጎት ተግባራት ከጊዜ ወደ ጊዜ ባሕል እየሆኑና በከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድም ከፍተኛ አድናቆትን እያተረፉ ይገኛሉ።

ይህ እንቅስቃሴ የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ፣ የነዋሪውን ማህበራዊ ትስስር በማጠናከር እና ለከተማዋ ያላቸውን የባለቤትነት ስሜት በእጅጉ በማሳደግ ላይ ይገኛል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በጎነትን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች መገለጫ አድርገው በተደጋጋሚ ያነሳሉ።

ደግነት ለሌሎች መትረፍ ብቻ ሳይሆን ራሳችንንም ጭምር የምናንጽበት፣ አብሮነታችንን የምናጠናክርበት ትልቅ ሀብታችን ነው ሲሉም ይናገራሉ።

ከተማዋ በኢኮኖሚ ከምታድገው በላይ በሰው አክብሮት እና በደግነት ልትታወቅ እንደሚገባም ይገልጻሉ።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በክረምት ወራት የሚከናወነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማሰባሰብ በጋራ ችግር ላይ በጋራ የመስራትን ባህል አጎልብቷል።

በተለይም ወጣቶች የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ፣ በአካባቢ ጽዳት፣ በውስጥ ለውስጥ መንገድ ጥገና እና የፍሳሽ ማስወገጃዎችን በመስራት የህዝቡን የዕለት ተዕለት ችግሮች በመቅረፍ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

ይህም የወጣቶችን የኃላፊነት ስሜት ከማሳደግ ባለፈ፣ ማህበረሰቡን በአንድነት የሚያስተሳስር ድልድይ ሆኗል።

በበጎ ፈቃድ ሥራዎች የታጀበው የአረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴም የአዲስ አበባን ገጽታ በአዲስ መልክ ቀርጾታል።

እንደ እንጦጦ-ቀጨኔ ወንዝ ዳርቻ ልማት ያሉ ፕሮጀክቶች፣ ነዋሪዎች ከተፈጥሮ ጋር ያላቸውን ቁርኝት እንዲያጠናክሩ አስችለዋል።

የበጎ ፈቃደኞች በየዓመቱ የሚያካሂዱት የችግኝ ተከላ፣ ህዝባዊ መናፈሻዎችን መንከባከብ እና አካባቢን ማልማት ከተማዋን ይበልጥ ምቹና ውብ እንድትሆን የራሱን አስተዋጽዎ አበርክቷል፡፡

የበጎ ፈቃድ ሥራው ቁሳዊ ድጋፍን ብቻ ሳይሆን፣ የሰውን አቅም የመገንባት ስራንም አቅፎ ይዟል።

በተለይም ለተማሪዎችና ለወጣቶች የሚሰጡ የአይቲ ክህሎት፣ የቋንቋ ስልጠና እና የሥራ ፈጠራ ስልጠናዎች የነገዋን አዲስ አበባ የሚረከብ ብቁ ትውልድ እየቀረጹ ነው።

በሌላ በኩል፣ የአገልግሎት አሰጣጡ በዲጂታል መንገድ እየተከናወነ መምጣቱ ቢሮክራሲን በመቀነስ፣ መልካም አስተዳደርን በማስፈን እና ለዜጎች ፈጣን አገልግሎት በመስጠት ረገድ ትልቅ ለውጥ እያመጣ ይገኛል።

ይህ ሁሉ ውጤት የተገኘው በግለሰቦች ተነሳሽነት ብቻ ሳይሆን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለህዝብ ተሳትፎ በሰጠው ትኩረትና በባለድርሻ አካላት መካከል በተፈጠረው ውጤታማ ጥምረት ነው።

በጎነትን መነሻ ያደረገው የሰው ኃይል በስራ ቦታውም ሆነ በቤተሰቡ ውስጥ ምርታማነትን በማሳደግ፣ ከተማዋን ለነዋሪዎቿ የተሻለች ማድረጉን ቀጥሏል።

በአጠቃላይ፣ የአዲስ አበባ የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራ የጋራ ችግርን በጋራ መፍታት እንደሚቻል በተግባር ያሳየ፣ ለከተማ ልማት ወሳኝ የሆነ የህዝብ ተሳትፎ ማሳያ እና የለውጥ መነሻ ነው።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

See less

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review