AMN – ሰኔ 9/2018 ዓ.ም

በፈረንሳይ በተካሄደው የቡድን-7 (G7) የሀገራት መሪዎች ጉባኤ ላይ የተገኙት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ እስራኤል በሊባኖስ ላይ እየወሰደች ያለውን እርምጃ ኮንነዋል፡፡
በአሜሪካና ኢራን መካከል የተደረሰዉን ስምምነት አስመልክቶ ፕሬዝዳንቱ በጉባዔዉ ላይ እንደገለጹት፤ የሆርሙዝ ወሽመጥ ያለ ምንም ክፍያ ለዓለም አቀፍ መጓጓዣ ክፍት ሆኖ ይቆያል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ስምምነቱ ኢራን በፍጹም የኒውክሌር መሣሪያ ባለቤት እንዳትሆን የሚያግድ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በዚሁ መድረክ ላይ ትራምፕ እስራኤል በሊባኖስ ላይ እየወሰደች ያለውን እርምጃ የኮነኑ ሲሆን፣ ይህም በአካባቢው ላይ አዲስ ዲፕሎማሲያዊ መነቃቃትን ፈጥሯል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል በተደረገው ድርድር ላይ እንደ ዋና ገላጋይ ሆና የቆየችው ፓኪስታን፣ ስምምነቱ እሁድ ዕለት መቋጫ ማግኘቱን በይፋ አውጃለች።
ምንም እንኳን የስምምነቱ ሙሉ ዝርዝር ይዘት እስካሁን ለሕዝብ ይፋ ባይደረግም፣ የትራምፕ አስተዳደር ባለሥልጣናት እንደገለጹት ሁለቱም ወገኖች በሰነዱ ላይ በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ወይም በዲጂታል መንገድ ፈርመዋል።
ይህ ይፋዊ እና ታሪካዊው የፊርማ ስነ-ስርዓት በዚህ ሳምንት መጨረሻ በጄኔቫ፣ ስዊዘርላንድ እንደሚከናወን ይጠበቃል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በአሜሪካና በኢራን መካከል የተደረሰዉን ስምምነት ተከትሎ በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ገበያ ላይ ፈጣን ተጽዕኖ ማሳደር የጀመረ ሲሆን የዓለም የነዳጅ ዋጋ ማሽቆልቆሉን ቀጥሏል።
የአንድ በርሜል የብሬንት ድፍድፍ ዘይት ዋጋ ከባለፈው መጋቢት ወር ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ80 ዶላር በታች ወርዶ መመዝገቡን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ወንድማገኝ አሰፋ