AMN- ሐምሌ 22/2018 ዓ.ም
በአሜሪካ መንግሥት የመካከለኛው ምስራቅ እና አፍሪካ ምክትል ረዳት ሚኒስትር ማርክ ሚቸል የተመራ ከፍተኛ ልዑክ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን ጎብኝቷል፡፡
በጉብኝቱ ወቅት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ያለውን የረጅም ዓመታት ታሪካዊ ግንኙነት በማስታወስ ኢንስቲትዩቱ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ የሚያከናውናቸውን ዋና ዋና ተግባራት በተመለከተ ለልዑካን ቡድኑ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ኢንስቲትዩቱ በሰው ሰራሽ አስተውሎት በቴክኖሎጂ ምርምር እና ልማት ስኬታማ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አስተረድተዋል።
በተለይም በተፈጥሮ ቋንቋ ቅንብር የኢትዮጵያን ሀገር በቀል ቋንቋዎች ለማሽን በማስተማር ረገድ ሀገሪቱ ለልዩ ልዩ ተግባራት መጠቀም መጀመሯን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ስታርታፖችን ለመደገፍ ኢትዮጵያ በልዩ ትኩረት እሰራች መሆኑን በመግለጽ በትብብር አብሮ ለመስራትም ምቹ ምህዳር መኖሩን አንስተዋል፡፡
በአሜሪካ መንግሥት የመካከለኛው ምስራቅ እና አፍሪካ ምክትል ረዳት ሚኒስትር ማርክ ሚቸል በበኩላቸው፤ ለተደረገላቸው አቀባበልና ገለጻ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ለስታርታፖች የሰጠውን ከፍተኛ ትኩረትና የሚያደርገውን ድጋፍም እንዳደነቁ የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያመላክታል፡፡
በሮቦቲክስ፣ በሆሎግራም ቴክኖሎጂ፣ በተፈጥሮ ቋንቋ ቅንብር እና በሌሎችም ዘርፎች ኢንስቲትዩቱ ያከናወናቸው ተግባራት ለአርአያነት የሚበቁ ናቸው ብለዋል።
ከጉብኝቱ ጎን ለጎንም ሁለቱ ሀገራት በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ዘርፍ በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ውይይት አካሂደዋል።