ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የመገናኛ ብዙኃን የንቅናቄ ዘመቻ አስጀመረ

You are currently viewing ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የመገናኛ ብዙኃን የንቅናቄ ዘመቻ አስጀመረ

AMN- ሰኔ 13/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሀገራዊ ምክክር ጉባኤውን ለማሳካት የሚያስችል የንቅናቄ ዘመቻ ለመጀመር ከመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለሞያዎች ጋር ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች አምባሳደር መሀሙድ ድሪር፣ ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያም እና ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) መገናኛ ብዙሀን ለኮሚሽኑ እስካሁን ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል።

ኮሚሽነሮቹ ቀጣዩ ሀገራዊ ጉባኤ ከቅድመ ጉባኤ ጀምሮ ጥንቃቄ የተሞላበት የአዘጋገብ ስልት እንደሚጠይቅ ገልጸው፣ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻ ለመጀመር መድረኩ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

መገናኛ ብዙሀን የሀገራዊ ምክክሩን ሂደት ሲዘግቡ በአካታችነት መርህ የሁሉንም ዜጎች ድምፅ እንዲያካቱ፣ የኮሚሽኑን ነፃና ገለልተኛ አሰራር እንዲጠብቁ እንዲሁም ለዘላቂ ሰላምና መግባባት በሚያግዝ መልኩ እንዲዘግቡ አፅንኦት ተሰጥቷል።

በተጨማሪም፣ መገናኛ ብዙኃን ከቅድመ እስከ ድህረ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ድረስ ትክክለኛ፣ ሚዛናዊ እና ተደራሽ መረጃ በማቅረብ ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።

በመድረኩ የመወያያ ፅሁፍ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል ሀላፊ ዮሀንስ ሽፈራው (ዶ/ር)፣ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን መገናኛ ብዙሀን ሊከተሏቸው የሚገቡ የአዘጋገብ ስልቶችና ሙያዊ ስነምግባሮችን ከዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ጋር አያይዘው አብራርተዋል።

የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎች በበኩላቸው፣ የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን ለሕዝብ በስፋት ለማስተዋወቅና መረጃዎች ተዓማኒነት እንዲኖራቸው በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በዕለቱ ኮሚሽኑ በራሱ የውስጥ አቅም ያዘጋጃቸውን 15 የክልል የምክክር መድረክ ዘጋቢ ፊልሞች፣ 19 የቴሌቪዥንና የማህበራዊ ሚዲያ የቅስቀሳ መልዕክቶችን፣ 6 የሬዲዮ መልዕክቶች እንዲሁም በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ አጫጫር መልዕክቶችን ለሚዲያ አመራሮቹ አስረክቧል።

እነዚህ መልዕክቶች ሚዲያዎቹ በራሳቸው አቅም ከሚያዘጋጇቸው ተጨማሪ ግብዓት ሆነው እንደሚያገለግሉ ተመላክቷል።

ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው መልዕክቶቹ ከመጪው ሰኞ ሰኔ 15/2018 ዓ.ም ጀምሮ በስፋት ወደ ሕዝብ እንዲደርሱ በኮሚሽኑና በመገናኛ ብዙሀኑ መካከል መግባባት ላይ ተደርሷል።

በንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረኩ ከ80 በላይ የሚዲያ አመራሮች፣ ከፍተኛ ባለሞያዎች፣ የመንግስት ተቋማት የኮሙኒኬሽን ኃላፊዎች እና የክብር እንግዶች ተገኝተዋል።

ኮሚሽኑ ባለፈው ሳምንት 50 የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሀን ኃላፊዎችንና ባለሙያዎችን በማሳተፍ ተመሳሳይ የሚዲያ ንቅናቄ ዘመቻ ማስጀመሩ ይታወሳል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review