አዲስ አበባ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ጨምሮ በተለያዩ የልማት ስራዎችና በሰላም ግንባታ ያስመዘገበችዉ ስኬት ለአፍሪካ ከተሞች ምሳሌ ሆኗል – አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር

You are currently viewing አዲስ አበባ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ጨምሮ በተለያዩ የልማት ስራዎችና በሰላም ግንባታ ያስመዘገበችዉ ስኬት ለአፍሪካ ከተሞች ምሳሌ ሆኗል – አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር

AMN ሰኔ 14/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ የኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎችን ጨምሮ በአረንጓዴ አሻራና በሰላም ግንባታ ያስመዘገበችዉ ስኬት ለሃገራችን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ተምሳሌት ሆኗል ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ”ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ቃል አካሂዷል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር; በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት ከሰባት አመታት በፊት በተጀመረዉ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸዉን ገልጸዉ መርሃ ግብሩ ለአካባቢ ጥበቃ ካበረከተዉ አስተዋጽኦ ባሻገር የአየር ንብረት ተጽእኖን በመከላከል ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንድትሆን አስችሏታል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የኮፕ 32 ጉባዔን እንድታዘጋጅ የተመረጠችዉም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ባመጣችዉ ለዉጥ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጥር በ2027 በኢትዮጵያ አዘጋጅነት አዲስ አበባ ላይ በሚካሄደዉ ኮፕ 32 ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባዔ ላይ ከ70 እስከ 80 ሺህ የሚደርሱ እንግዶች እንደሚታደሙ የገለጹት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር መድረኩ በአዲስ አበባ መካሄዱ ለሃገራችን ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የአረንጓዴ እና የአካባቢ ጥበቃ ስራ አዲስ አበባን ጨምሮ በመላዉ ሃገሪቱ ተቋማዊ አሰራር ሆኖ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት አፈ ጉባዔዉ አረንጓዴ አሻራ ያመጣዉን ለዉጥ ለመረዳት የአዲስ አበባ ወንዞች የነበሩበትን ሁኔታ ማስታወስ በቂ ነዉ ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመዲናዋ ያከናወነዉ ትርጉም ያለዉ የልማት ስራ ለሃገራችን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ተምሳሌት ነዉ ያሉት አፈ ጉባዔዉ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ በየደረጃዉ የሚገኙ የከተማዉ አመራሮች ያለምንም ድካም ለህዝብ ራሳቸዉን በመስጠት ላበረከቱት አስተዋጽ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

አዲስ አበባ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎችን ጨምሮ በሁሉም ዘርፍ ተወዳዳሪ እና በአፍሪካ ደረጃ የምትጠቀስ ከተማ በመሆን ላይ እንደምትገኝ የተናሩት አፈ ጉባዔዉ መዲናዋ አስተማማኝ ሰላም በመገንባት ረገድ ያሳየችዉን ለዉጥ አጠክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡

ተስፋን እንትከል በሚል መሪቃል ዘንድሮዉ በሚካሄደዉ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ የመዲናዋ ባለሃብቶች፤ የመንግስትና የግል ተቋማት እንዲሁም መላዉ የመዲናዋ ነዋሪዋች ችግኝ በመትከልና በመንከባከብ ለትዉልድ የሚተርፍ አሻራቸዉን እንዲያኖሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review